ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሉዓላዊነቷ የሚቆሙ ልጆች አጥታ አታውቅም - ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ

ሀዋሳ፤ መስከረም 26/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጪ ሆነው ለመቦርቦር የሚሞክሩ አካላት ለአገር ሉዓላዊነት ማስከበር የሚቆሙ ልጆች አጥታ እንዳማታውቅ ማወቅ እንደሚገባቸው ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ገለጹ።

የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በሁለተኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች ዛሬ አስመርቋል።

የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከፍተኛ ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምእሸት ደግፌ ይህን ያሉት ዛሬ የብላቴ ኮማንዶና አየር ሃይል ማስልጠኛ ማዕከል መሠረታዊ ወታደሮችን ባስመረቀበት ወቅት ነው።

ሌቴናል ጄኔራል ዓለምእሸት በዚሁ ወቅት ለተመራቂዎቹ "አገርን ከውስጥም ሆነ ከውጪ ዘብ ሆናችሁ ለመጠበቅ ወስናችሁ የተሰለፋችሁ ናችሁና በአድራጎታችሁ ልትኮሩ ይገባል" ብለዋል።

እናንተ የኢትዮጵያ ወታደሮች ናችሁ፤ የቆማችሁት ሁሉንም ህዝባችንን እኩል ዓይታችሁ ጸጥታውን ልታስከብሩለት ነው ብለዋል።

የምትሰማሩበት ተልዕኮ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስጠበቅ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ለኢትዮጵያ ክብሯንና አንድነቷን ለማስጠበቅ የቆማችሁ የቁርጥ ቀን ልጇቿ ናችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ቃል መግባታቸውን ያወሱት ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት፤ ቃል ገብታችኋል፤ ከአሁን በኋላ መለዮ ለባሽ መሆናችሁን ያረጋገጣችሁ ወጣቶቻችን ልዩ ናችሁ። የተለየ ፍቅርና ክብር ይገባችኋል ብለዋል።

ህዝብና አገርን ለመከላከልና ለመጠበቅ በምትሰሩት ስራ ነገ ከህዝብ ፊት በኩራት የምትቆሙ፤ ሁሉም የማይታደለው የትውልዱ ተምሳሌት ምልክቶች ትሆናላችሁ ሲሉም አስረድተዋል።

ዛሬም የአገርን ድንበርና አንድነት ለማስጠበቅ መከላከያን እየተቀላቀሉ መሆኑን ያነሱት ሌተናል ጀኔራሉ፤ አገርን ከውስጥና ከውጪ ሆነው ለመቦርቦር የሚሞክሩ አካላት ኢትዮጵያ ለአገርና ለሉዓላዊነቷ የሚቆሙ ልጆች እንዳሏት ማወቅ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ኮለኔል ቦጃ አጋ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ የተሰጣቸውን ስልጠና በስኬት ማጠናቀቃቸውንና በሚመደቡበት የስራ መስክ በታማኝነትና በጀግንነት ግዳጃቸውን መፈጸም የሚያስችላቸውን ብቃት እንደያዙ ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ በተመደቡበት ክፍል ልምድ በመውሰድና አቅማቸውን የበለጠ በማዳበር ተቋሙ የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በታታሪነትና በላቀ ጀግንነት መፈጸም እንዳለባቸው በማሳሰብ።

ማዕከሉ በውስጡ የኮማንዶ፣ የአየር ወለድ ማሰልጠኛ፣ የልዩ ሃይል ጸረ ሽብር ማሰልጠኛና የአመራር ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም