ተቋምን ብሎም ሀገርን ለማገልገል በቅድሚያ ጥብቅ በሆነ ሙያዊ ዲሲፕሊን መታነፅ ያስፈልጋል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋምን ብሎም ሀገርን ለማገልገል በቅድሚያ ጥብቅ በሆነ ሙያዊ ዲሲፕሊን መታነፅ ያስፈልጋል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2017(ኢዜአ)፦ ተቋምን ብሎም ሀገርን ለማገልገል በቅድሚያ ጥብቅ በሆነ ሙያዊ ዲሲፕሊን መታነፅ ያስፈልጋል ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰልጣኝ የበረራ አስተናጋጆችን በአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ተቀብለው አነጋግረዋል።
አዛዡ በዚህ ወቅት ሀገርን ብሎም ተቋምን ለማገልገል በቅድሚያ የሀገር ፍቅር ስሜት ከአላማ ፅናት ጋር መላበስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የእርስ በእርስ መደጋገፍን እንደባህል መያዝ እንደሚገባ እና ከፋፋይ ከሆኑ ጎጂ አስተሳሰቦችም መራቅ ወሳኝ ነጥብ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የበረራ አስተናጋጆች ውስጣዊ አንድነታቸውን ይበልጥ በማጎልበት ከብሔርተኝነት ከሃይማኖት አክራሪነት እንዲሁም ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ራሳቸውን ማራቅ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስተንግዶ ኃላፊና አሰልጣኝ መምህርት መሰረት ገላየ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተሰጠው ሀገራዊ ተልዕኮ ባሻገር እየሰራ ያለው የልማት ስራ ለሌሎችም ተቋማት መልካም አርዓያ መሆኑን አውስተው፤ ለዚህ የተቋሙ ስኬት ሚናቸውን ለተወጡ የሰራዊቱ አመራሮች እና አባላት ትልቅ ክብር እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዕለቱም የአየር መንገዱ የበረራ መስተንግዶ ሰልጣኞች የኢትዮጵያን አየር ኃይል ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።