ሁለተኛው የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
ሁለተኛው የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ

ድሬዳዋ፤ መስከረም 26/2017(ኢዜአ)፡- የአርብቶ አደሩን ህይወት ከተረጂነት ለማላቀቅ የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት መጀመሩን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ገለፀ።
በድሬዳዋ አስተዳደር የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በድሬዳዋ በተካሄደው በሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የቆላማ አካባቢዎችና መስኖ ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ የዓለም ባንክ ተወካዮች እና ፕሮጀክቱ የሚመለከታቸው የድሬዳዋ የካቢኔ አባላት ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት በሚኒስቴሩ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ አቶ ሰዒድ ኡመር እንዳሉት፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕሮጀክቱ አተገባበር የአርብቶአደሩን ህይወት ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያግዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍም የድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ በስምንት የአገሪቷ ክልሎች በሚገኙ 120 ወረዳዎች የአርብቶ አደሩን ህይወት የሚያሻሽሉ የልማት ስራዎች በ424 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይተገበራል።
ከ2024 እስከ 2029 እ.ኤ.አ ለአምስት አመት በሚተገበረው በዚሁ ፕሮጀክት ሶስት ሚሊዮን ቤተሰቦች በቀጥታ እና ሁለት ሚሊዮን ደግሞ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመግለፅ።
የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች የሚሆኑትም በተለይም የአርብቶ አደር ሴቶችና ወጣቶች ለሚያነሷቸው የስራ ጥያቄዎች በተለያዩ የገቢ ማግኛ ስራዎች ተሳተፈው ተገቢውን ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።
የሚከናወኑት የልማት ተግባራትም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የእንሰሳት ሃብት ልማት እና ሌሎች መሠረታዊ የመሠረተ ልማት ስራዎች ሲሆኑ፤ ይህም የአርብቶ አደሩን ህይወት በማሻሻል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናውን በዘላቂነት እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው አስተዳደሩ የሁለተኛው ምዕራፍ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆኑ በገጠሩ አራት ክላስተሮች የሚገኙ አርብቶ እና ከፊል አርብቶአደሮችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በማሸጋገር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ ያስችላል ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደርም ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ በመግለፅ።