በስነ ምግባርና በእውቀት የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር በንባብ ባህል ላይ በትኩረት መስራት ይገባል

ዲላ ፤መስከረም 26/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ በስነ ምግባርና እውቀት የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ከግብ እንዲደርስ የንባብ ባህል ማዳበር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት  አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሳምንቱ በፓናል ውይይት፣ በመጽሐፍ ስርጭት እንዲሁም ቤተ መጽሐፍ ማቋቋምና የተለያዩ ኩነቶችን ባካተቱ መርሃ ግብሮች እየተካሄደ ነው። 

የአገልግሎቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባተ ካሳው በወቅቱ እንደገለጹት፤ በስነ ምግባርና እውቀት የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያስችል ስራ ማከናወን ያስፈልጋል።  

በትምህርት ከሚገኘው እውቀት በተጓዳኝ በማንበብ የትምህርት ውጤት ለማስተካከልና ስብራትን ለመጠገን የሚያስችል እድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

መጻሕፍትን በማንበብ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቀቶች እያዳበሩ መሄድ እንደሚያስችል አመልክተው፤ ለዚህ ደግሞ "የንባብ ባህልን ማጠናከር ተኪ የለውም"  ብለዋል።

አገልግሎቱ የንባብ ባህል ለማዳበር የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት ጥረት እያደረገ እንደምገኝ ጠቅሰው፤ አብያተ መጻሕፍትን በመያዝ በየዓመቱ በአስር ከተሞች መሰል መርሐ ግብር እያካሄደ መሆኑን አቶ አባተ ተናግረዋል።

በዚህም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማንበብ ባህላቸውን እንዲዳብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለይርጋጨፌ ከተማ 660 መጻሕፍትን ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። 

"የአገራት የእድገት ልዩነት የንባብ ባህል ነው" ያሉት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ተወካይ ዓለማየሁ አካሉ(ዶ/ር) ናቸው። 

የአገርን ጸጋና ባህል ለትውልድ ለማስተላለፍ የንባብ ባህል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ለዚህም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በከተማዋ የንባብ ባህል መቀዛቀዝ በተማሪዎች ውጤት ላይ ጫና ማድረሱን ጠቅሰዋል ።

ይህንን ችግር ለማቃለል በተለይም ለትምህርት ስብራት ምላሽ ለመስጠት የባለድርሻዎችን ተሳትፎ በማጠናከር በተማሪዎች የንባብ ባህል ላይ በትኩረት  እየሰሩ መሆናቸው ገልጸዋል ።

መርሃ ግብሩ የተጀመረው መሰል ጥረቶች እንዲጠናከሩ መነቃቃት ለሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመርሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ ነው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም