ቀጥታ፡

የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 26/2017 (ኢዜአ)፦ የ24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ዛሬ በታንዛንያ ይጀመራል።

በማጣሪያ ውድድሩ ላይ ዘጠኝ አገራት ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያ በማጣሪያው በምድብ 2 ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ ከዩጋንዳ ጋር ያደርጋል።

20 ተጫዋቾችን የያዘው ስብስብ ከትናንት በስቲያ ዳሬሰላም መግባቱ ይታወቃል።

ቡድኑ የመጀመሪያ ልምምዱን ትናንት ኪጋምቦኒ በሚገኘው የታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስልጠና ማዕከል ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በማጣሪያው በምድብ አንድ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።

የውድድሩ አዘጋጅ ታንዛንያ ከኬንያ ዛሬ ከቀኑ 10 ላይ በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስል ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በዚሁ ምድብ ሱዳን ከጅቡቲ ከምሽቱ 12 ሰዓት በአዛም ኮምፕሌክስ ይጫወታሉ።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም