ደጋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በማሻሻል የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ መቀየር ይገባል - ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ መስከረም 26/2017(ኢዜአ)፦ ደጋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በማሻሻል የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ መቀየር እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ። 

በክልሉ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የምዕራፍ ሁለት ፕሮግራም ማስጀመሪያ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል። 


 

ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ዓለሚቱ በማስጀመሪያ መድረኩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ደጋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በማሻሻል የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለመለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል። 

የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በክልሉ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።

በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሚተገበረው በሁለተኛው ዙር የቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክትም በተመሳሳይ መልኩ ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚከናወኑበት እምነታቸውን ገልፀዋል። 

በመሆኑም የልማት ፕሮጀክቶቹን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የማህበረሰቡን ህይወት ለመለወጥ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የክልሉ መንግስትም ዛሬ ይፋ ለተደረገው የሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ስኬታማነት የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሯ ገልፀዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ኡቶው ኡኮት በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ መንግስት ለጀመራቸው የልማት ስራዎችን በማገዝ ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። 

ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ በክልሉ ስምንት ወረዳዎች የተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጹት ደግሞ በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የጋምቤላ ክልል አስተባባሪ ቤል ቤቾክ(ዶ/ር) ናቸው። 


 

በፕሮጀክቱ በተከናወኑት የልማት ስራዎችም ከ180 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል። 

ፕሮጀክቱ በሁለተኛው ምዕራፍ በ2017 በጀት ዓመት ለሚተገብረቸው የመንገድ፣ የትምህርት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ማስፈፀሚያ ከ407 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንም አብራርተዋል። 

የሁለተኛው ምዕራፍ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተያዘውን በጀት ዓመት ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በክልሉ ዘጠኝ ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ በመድረኩ ላይ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም