ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት  ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት  እንዲሰጥ ተጠየቀ

ጋምቤላ ፤ መስከረም 25 ቀን 2017  (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የመሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መንግስት በትኩረት እንዲሰራ በክልሉ የኑዌር ዞን ነዋሪዎች ጠየቁ።

ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገልጸዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ የተካሄደውን ህዝባዊ የሰላምና  የልማት  ኮንፈረንስ አጠናቀዋል ።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ሜሪ ኛዋል በሰጡት አስተያየት፤ “አዲሱ አመራር በዞናችን  ብሎም በክልሉ ሰላምን  በማስፈን ረገድ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው” ብለዋል። 


 

አዲሱ አመራር በቀጣይ በአኮቦና ሌሎች አካባቢው ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራዎችን ማከናወን እንዳለበት አመልክተዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ አዲሱ የለውጥ አመራር እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት በመሰረተ ልማት ግንባታም አጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የተናገሩት የኮንፈረንስ ተሳታፊ ኡቻላ ኡቀይ ናቸው።

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ አወር ኡፒዮው በበኩላቸው፤  ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሌሎች ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል አመልክተዋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መንግስት እየሰራ ነው።  


 

“የልማትና የመልካም  አስተዳዳር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው አሁን ላይ ያለው ሰላም ዘላቂነቱ ሲረጋገጥ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለአካባቢው ሰላም ዘብ ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በፌዴራል እና በክልል መንግስት በኩል በጠረፍማ ወረዳዎች ያሉትን የመንገድና የሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

በክልሉ በተዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋለው የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ የክልሉ  መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በክልሉ አስተማማኝ  ሰላም ሊሰፍን የቻለው “ሰለም ወዳዱ ህዝብ ባደረገው የተቀናጀ ጥረት ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን ናቸው።

በቀጣይም ህዝቡ የጀመረውን የሰላም ግንባታ በማጠናከር ለክልሉ ልማትና እድገት በአንድነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በኑዌር ብሔረሰብ ዞን በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ ለአንድ ቀን  ወቅታዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ሲካሂዱ የዋለው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ማምሻውን ተጠናቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም