በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ አጀንዳ ለማሰባሰብ የተጀመረው የምክክር መድረክ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ አጀንዳ ለማሰባሰብ የተጀመረው የምክክር መድረክ እንደቀጠለ ነው
ሰመራ ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ለማሰባሰብ በአፋር ክልል ከባለድርሻ አካላትና ከተመረጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እያካሄደ ያለውን ምክክር ቀጥሏል።
ምክክሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን የሚወጡበትና አጀንዳቸውን የሚያስቀምጡበት መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ሳሊህ አህመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ለመወጣትና አጀንዳቸውን ለማስቀመጥ የሚያስችላቸው ነው።
የምክክር ምዕራፉ አንድነትና መስማማትን የሚያመጣ ከመሆኑም በላይ ተሳተፊዎች እርስ በርስ በመነጋገር ጠቃሚ ሀሳቦችን እንዲያፈልቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ግጭቶችን ከሚፈጥሩ አባዜዎች ወጥቶ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሀገራዊ ምክክሩ የጎላ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
ትውልዶች የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀምና ወደጠረጴዛ በመምጣት ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመፍታት ባህልን እንዲያዳብሩ የሚያስችል መሆኑንም አስታውቀዋል።
ይህንን ታሪካዊ ሂደት በአግባቡ መጠቀም የጎላ ፋይዳ አለው ሲሉም አስተባባሪዋ ገልጸዋል።
አራተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ መድረክ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች፣ በአገር አቀፍና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ተፅፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም በክልሉ በጎ አሻራ ያሳረፉ ግለስቦች እየተሳተፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ በአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ እየተካፈሉ ያሉት ከ800 በላይ ባለድርሻ አካላት ናቸው።
ተሳታፊዎቹ በአምስት ቡድኖች ተከፋፍለው በየቡድናቸው በነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተወያዩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሰመራ ከተማ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም የተጀመረውን ምክክር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባና የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) ማስጀመራቸው የሚታወስ ነው።