በኢሬቻ በዓል የታየው አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢሬቻ በዓል የታየው አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ)፦ በኢሬቻ በዓል የታየው አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።
የ2017 ዓ.ም ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዓሉን ለመታደም ከመጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
ካነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ከሲዳማ ክልል የመጡት አቶ ዳቢስ ሸንጊሶ፤ ኢሬቻ እኛ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ከሚያስተሳስሩን እሴቶቻችን መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
ኢሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ የሚተዋወቁበትና ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው ብለዋል።
በዓሉ መነሻው የኦሮሞ ሕዝብ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀውና በድምቀት የምናከብረው የጋራ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት።
ይህንን የኢትዮጵያ ኃብት የሆነውን በዓል በጋራ ልናከብረው እና ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።
በበዓሉ ያሳየነውን አንድነትና ወንድማማችነት በልማቱም ላይ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈን ልንደግመው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከሀላባ ዞን የመጡት አቶ ከማል ሐሰን በበኩላቸው፤ ኢሬቻ የሰላም፣ የወንድማማችነት ማጠናከሪያ በዓል ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሁላችንም የዚህች አገር የዘመኑ ባላደራዎች እንደመሆናችን መጠን አንዳችን የሌላችንን ባህል በመውደድና እርስበርስ በመዋደድ ልንኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ በዓል ላይ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን በግልጽ ተመልክቼበታለሁ ያለው ደግሞ ከአርባ ምንጭ የመጣው አቤል አማረ ነው።
ሌላኛው ከሃድያ ዞን የመጡት አቶ መስፍን ቦጋለ፤ ኢሬቻ የሰላም፣ የምስጋና የወንድማማችነትና የፍቅር በዓል መሆኑ መጥተን ከወንድሞቻችን ጋር እንድናከብረው አድርጎናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሕዝብም እጅግ ሰው ወዳድና ሰው አክባሪ መሆኑን በዚህ በዓል ላይ በተግባር አሳይቶናል ብለዋል፡፡