ቀጥታ፡

ኢሬቻና የበዓሉ ታዳሚዎች

ከገዳ ሥርዓት እሴቶች አንዱ የሆነው የኢሬቻ በዓል ዘንድሮ "ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ" በሚል መሪ ሀሳብ በሆራ ፊንፊኔ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሯል።

በአባመልካና በአባገዳዎች ምርቃት በተጀመረው በዓል ላይ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና  የውጭ ሀገራት ዜጎች ተገኝተዋል። 

የበዓሉ ታዳሚዎች እንደሚሉት ኢሬቻ በአሁን ወቅት እያደገ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም እየታወቀ በመሆኑ መደሰታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ገልፀዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ትዕግስት መኮንን እንደገለፁት፤ ኢሬቻ የኢትዮጵያ ሕብር የሚገለጥበት ጌጥ በመሆኑ ልንኮራበትና ይበልጥ ልናጎለብተው ይገባል  ሲሉ ተናግረዋል።

የሕዝብን አንድነት የሚያጠናክር ኃብት የሆነውን የኢሬቻ በዓል እሴቱ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

በዓሉ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት የተጠናቀቀ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለቀጣይ ዓመት በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ለማክበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡  

ሌላው ታዳሚ   መብራቱ ቶሎሳ እንደገለፀው፤ ሆራ ፊንፊኔ  የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያ ሕዝብ  ትስስርንና አንድነትን እያጠናከረ ነው፡፡


 

ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጭ የሚመጡ እንግዶች በጋራ ተሰባስበው የሚገናኙበት ታላቅ ሁነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ተሬሳ አያና በበኩሉ፤ ከኢሬቻ ክብረ-በዓል  በኋላ ሕብረታችንን አጠናክረን በሰላም መኖራችንን ማስቀጠል አለብን ብሏል።


 

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እንደቀየረው በመግለጽ፤ በቀጣይ እጅ ለእጅ ተያይዘን የአገራችንን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆን አለብን ሲልም አክሏል።


 

መምህር  ሎሜ ገብረማርያም፤ ኢሬቻ ለተከታታይ ዓመት ማክበራቸውን ገልጸው፤ የዘንድሮ ዓመትም ድባብ ከከተማው አዲስ ገጽታ ጋር ተዳምሮ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ልብነሽ ስንታየሁ በበኩሏ፤ የኢሬቻ በዓል ሁሉም ያለውን ለብሶ አምሮና አጊጦ የሚወጣበትና ባህሉን በአንድነት በመሆን የሚያስተዋውቅበት መሆኑን ገልጻለች፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም