ቀጥታ፡

ኢሬቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ማቆየት ይገባል - የበዓሉ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ)፦ የወንድማማችነትና የሕዝቦች ትስስር የበለጠ የሚጠናከርበት የኢሬቻ በዓል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ባህላዊ እሴቱን ሊጠበቅ እንደሚገባ የሆራ ፊንፊኔ በዓል ተሳታፊዎች ገለጹ።

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በርካታ ህዝብ በተገኘበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በአባ መልካ እና በአባ ገዳዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበዓሉ ታድመዋል።

ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአብሮነትና ወንድማማችነትን እንዲሁም የሕዝቦች አንድነትና ትስስር የበለጠ የሚጠናከርበት ነው።

ሊቀ ትጉሃን ዘነበ አለማየሁ በኢሬቻ ላይ ያለ ምንም የሃይማኖት ልዩነት ሁሉም የሚሳተፍበትና የሕዝብ አንድነት የሚጠናከርበት በመሆኑ ባህላዊ እሴቱ ተጠብቆ ሊቆይ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አባቶቻችን የወንድማማችነት፣ የሰላምና የአብሮነት እሴቱን ጠብቆ ለዛሬ አድርሰዋል አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ ባህላዊ እሴቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ የገዳ ሥርዓት አካል የሆነና ድንቅ የሆነውን ባህል እሴቱን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ አለበት ሲሉም ጠቁመዋል።

ከወንድም የኦሮሞ ሕዝብ ጋር በኢሬቻ በዓል ላይ ለመሳተፍ ከጌዲዮ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ተክሉ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲቆይ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

በታላቅ ድምቀት ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያከብሩት የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱ እንዲጠበቅና የበለጠ እንዲተዋወቅ እኛም የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ነው ያሉት።

ሌላው የኢሬቻ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ይስሐቅ ተክሉ በበኩላቸው፤ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገራት እሴቱን ለማየት የሚሳተፉበት ይህ በዓል ተጠብቆ ሊቆይ ይገባል ብለዋል።

ኢሬቻ የሕዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር፣ መተዋወቅ እና የባህል ልውውጥ የበለጠ የሚጠናከርበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ተስፋዬ ቤካ ወጣቶች በጉጉትና በፍቅር የሚጠብቁት እና የሰላም እሴቱ የሆነው ኢሬቻ ሁሉም ሊጠብቀው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም