በተለያዩ ሕብረ-ቀለማት ያጌጡ የባህል አልባሳት የታየበት የኢሬቻ በዓል - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ሕብረ-ቀለማት ያጌጡ የባህል አልባሳት የታየበት የኢሬቻ በዓል

የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በድምቀት ተከብሯል።
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በአባ መልካና በአባ ገዳዎች ምርቃት ተጀምሮ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።
ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአብሮነትና ወንድማማችነትን እንዲሁም የሕዝቦች አንድነትና ትስስር የበለጠ የሚጠናከርበት ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢሬቻ በዓል በተለያዩ ዲዛይኖችና ቀለማት ያማሩ አልባሳት የሚታይበት መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ከተሳተፉት መካከል አቶ ኃይሉ አበበ እንዳሉት፤ በበዓሉ ላይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በየዓመቱ እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።
ኢሬቻ ወንድማማችነትና አብሮነት ጎልቶ የሚታይበት በመሆኑ፤ እነሱም በቡድን በዲዛይን የተሰሩ ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የተለያዩ አካባቢዎች ባህላዊ አልባሳት በፋሽን እንዲታዩ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
በኢሬቻ በዓል ላይ የተሳተፉ ሌሎች ሰዎች በበኩላቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሕብረ-ቀለማት በበዓሉ እንደሚታይ ተናግረዋል።
እነሱም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ተመሳሳይ የባህል አልባሳትን በመልበስ እንደተሳተፉ ገልፀዋል።
ሰዎች በሕብረት በመሆን የባህል አልባሳት እየለበሱ መሳተፋቸው ለኢሬቻ በዓል ተጨማሪ ድምቀት እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።