ቀጥታ፡

በትምህርት ልማት የተመዘገቡ ለውጦችን በማጠናከር የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት ቅንጅታዊ ጥረት ያስፈልጋል

ዲላ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ):- በትምህርት ልማት እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን በማጠናከር የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት ቅንጅታዊ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ገለጸ።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ትምህርት ቤቶችን ሳቢና ምቹ የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ እንደገለጹት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትምህርት ልማቱ ላይ የተጀመረው ጥረት መጠናከር ይኖርበታል።

 

ስርዓተ ትምህርት ከመቀየር ጀምሮ የግብዓትና የመምህራን አቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚያግዙ የማሻሻያ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህም በቀጣይ የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፣ መምህራን የሚያነሷቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

ባለፉት ዓመታት በትምህርት ልማቱ የተመዘገቡ ለውጦችን በማጠናከር የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በክልሉ የመምህራን ያልተፈቱ ጥያቄዎች በትምህርት አሰጣጥና በተማሪዎች ውጤት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ታደለች ኡርቆ ናቸው።


 

መምህራን ችግሮችን በመቋቋምና ራሳቸውን በማብቃት የትምህርት ስብራቱን የመጠገን ግንባር ቀደም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአሌ ዞን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ሂሩት አብጤ በበኩላቸው የትምህርት ስብራትን በተለይ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የመምህርነት ሚናቸውን ለመወጣት እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የትምህርት ልማት ለአንድ ወገን የሚጣል አይደለም የሚሉት መምህርት ሂሩት በትምህርት ልማቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማጠናከር የትምህርት ስብራቱን ለመቀልበስ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በክልሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን ብቃትን መሰረት ያደረገ የትምህርት አመራር ምደባ ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው።


 

መምህራን የሙያ ብቃታቸውን ለማሻሻል መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ወደው እንዲከታተሉ ትምህርት ቤቶችን ሳቢና ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከርም አስገንዝበዋል።

ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የሚደረገውን ጥረት መምህራን በግንባር ቀደምትነት እንዲያግዙም አመልክተዋል።

በክልሉ መምህራን የሚያነሱትን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር የምስረታ ጉባኤ በዲላ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በጉባኤውም የትምህርት ጥራትና የተማሪዎች ውጤት ማሻሻል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት መደረጉ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም