የ2017 የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም ተጠናቋል - ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የ2017 የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም ተጠናቋል - ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ):- በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብና አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እና ከጎረቤት ሀገራት የመጡ እንግዶች እንዲሁም የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የታደሙበት የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር በመቀናጀት አስቀድሞ የስጋት ቦታዎችን ለይቶ በማጥራት በቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል አሰማርቶ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ፣ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ከሰላም ሠራዊት ወጣቶች ጋር ተባብሮ በመሥራት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ገልጿል፡፡
የበዓሉ በሰላም መጠናቀቅ ለሀገራችን መልካም ገፅታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ድርሻቸውን በሚገባ ለተወጡ ለአባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች፣ ለበዓሉ ታዳሚዎች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣ ለበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች እና ለሰላም ሠራዊት ወጣቶች እንዲሁም በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃትና በትጋት ለተወጡ የፀጥታና ደኅንነት አካላት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የላቀ ምስጋና ማቅረቡን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓልም ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ ለፀጥታና ደኅንነት አካላት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡