የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የመከባበር ኃይል የሚያሳይ ትልቅ መሰባሰቢያ መድረክ ነው - የበዓሉ ታዳሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የመከባበር ኃይል የሚያሳይ ትልቅ መሰባሰቢያ መድረክ ነው - የበዓሉ ታዳሚዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2017(ኢዜአ):- የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የመከባበር ኃይል የሚያሳይ ትልቅ መሰባሰቢያ መድረክ ነው ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ገለጹ።
በበዓሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በባህላዊ አልባሳት አጊጠው አዲስ አበባ የተገኙ በርካታ ሰዎች በሆራ ፊንፊኔ በመሠባሠብ የኢሬቻ በዓልን እያከበሩ ነው።
በበዓሉ ላይ የተገኙት አቶ መብራቱ ቶሎሳ እንደገለፁት ሆራ ፊንፊኔ የኢትዮጵያዊያንን የአንድነትና የመከባበር ኃይል የሚያሳይ ትልቅ የመሰባሰቢያ መድረክ ሆኗል።
ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከአገር ውጪ የሚመጡ እንግዶች በጋራ ተሰባስበው የሚገናኙበት ታላቅ ሁነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል ሁሉም ያለውን ውበት አጉልቶ የሚያወጣበትና የሚያስተዋውቅበት መሆኑን ተከትሎ ያማረ የኢሬቻ በዓል በመከበሩ መደሰታቸውን ነው የገለጹት፡፡
ሌላኛዋ የበዓሉ ታዳሚ ነቢሲ ጠሬሳ ኢሬቻ ላይ የታየው ሰላምና አንድነት በመላው ህዝብ ዘንድ እንዲጋባ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡
በዓሉ ሰላምን በማስፈንና ልማትን በማረጋገጥ ከድህነት ለመውጣት የሚያስችል ርብርብ ለማድረግ የሚያነሳሳ ነው ብላለች፡፡
ከዛሬ በኋላ ህብረታችንን አጠናክረን፣ ጥላቻ አስወግደን በሰላም አብሮ የመኖር ባህላችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን በማለት ነው የተናገረችው።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እንደቀየረው በመግለጽ በቀጣይ እጅ ለእጅ ተያይዘን የአገራችንን ሰላምና ብልፅግና ልናረጋግጥ ይገባል ስትል ተናግራለች፡፡
አቶ ዝናቡ ኃይሉ በበኩላቸው በየዓመቱ በበዓሉ ላይ እንደሚታደሙ ገልጸው ህብረተሰቡ ካለፉት አመታት ልምድ በመውሰድ የዘንድሮው በዓል ድባቡ የተለየና ያማረ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይም በዓሉ እሴቱን ጠብቆ ከልጅ እስከ አዋቂ በመልካም ስነምግባር በዓሉን እንዳከበሩ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ያዳረጉት አቀባበል ማራኪ መሆኑን በመመስከር ለተደረገላቸው ሁሉ አመስግነዋል።
የዘንድሮው የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ''ኢሬቻ ለባህላችን ሕዳሴ'' በሚል መሪ ሃሳብ በኅብረ ቀለማት ባሸበረቀ መልኩ በመከበረ ላይ ይገኛል።