ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በዓለም አቀፍ የሮቦት ኦሊምፒያድ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በዓለም አቀፍ የሮቦት ኦሊምፒያድ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በሕዳር ወር በተርኪዬ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሮቦት ኦሊምፒያድ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሳተፉ ተገለጸ።
ኦሊምፒያዱ ወጣቶች የሮቦት ፈጠራ ስራቸውን በማቅረብ የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑ ተመላክቷል።
ለዚህ አለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፈው የሮቦቲክ የፈጠራ ውጤት የማወዳደር መርሃ ግብር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዛሬ ተካሂዷል።
በአዲስ አበባና ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የስቲም ፓወር ማዕከል ተማሪዎች በግብርና፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪ፣ ከተማ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ 37 የሮቦቲክስ የፈጠራ ውጤቶችን ለውድድሩ አቅርበዋል።
ከእነዚህ መካከል ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እንዲሁም በጤና ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጥ የሮቦት ፈጠራ ውጤት ያቀረበው ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል በውድድሩ እንዲሳተፍ ተመርጧል።
የቡድኑ ተወካይ የ11ኛ ክፍል ተማሪ በረከት አሰፋ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ፣ በሕክምና እንዲሁም በግብርና የምታከናውነውን ተግባር ለማቀላጠፍ የሮቦት የፈጠራ ውጤቱን ለመስራት እንደተነሳሳ ገልጿል።
ተማሪዎቹ በተርኪዬ በሚካሄደው የአለም ሮቦት ኦሊምፒያድ ውድድር በዲጂታል ዘርፍ ሀገራቸውን ለማስጠራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የስቲም ፓወር ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ስሜነው ቀስቅስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን በመወከል በዓለም ሮቦት ኦሊምፒያድ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ተማሪዎች ለማዘጋጀት በ40 የስቲም ፓወር ማዕከላት ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል በችግር ፈቺነቱና ለዓለም አቀፍ መድረክ ብቁ በመሆኑ የተመረጠውና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የፈጠራ ውጤት ለውድድሩ ከመቅረቡ በፊት ለገበያ ብቁ የማድረግ የማሻሻያ ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ መሳተፏ የቴክኖሎጂና ፈጠራ አቅሟን የምታሳይበትና ለተማሪዎች አለም አቀፍ እድሎች የሚፈጠሩበት እንደሚሆን አመልክተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ዲጂታል ምጣኔ ሃብትን እውን ለማድረግ ለፈጠራና ምርምር ምቹ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ዩኤንሲኤ) ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው አፍሪካ በቴክኖሎጂ ከአለም ጋር ለመወዳደር ለዲጂታል ትምህርት ትኩረት መስጠት እንዳለባት አስገንዝበዋል።
በወጣቶች ላይ የፈጠራ ክህሎትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት አጀንዳ 2063ን እውን በማድረግ የአፍሪካን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የ2024 ውድድር እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከህዳር 28 እስከ 30/2024 በተርኪዬ ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ ከ80 ሀገራት በላይ እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።
የዓለም ሮቦት ኦሊምፒያድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2004 የተጀመረ ውድድር ነው።