በጋምቤላ ክልል የኮደርስ ስልጠናን ሰኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የኮደርስ ስልጠናን ሰኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል
ጋምቤላ፤ መስከረም 24/2017 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የኮደርስ ስልጠናን ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና ባለድርሻዎች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ አስገነዘቡ ።
በጋምቤላ ከተማ "የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ'' የክልል ዕቅድ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በአገር ደረጃ የተያዘው የዲጂታላይዜሽን ስልጠና መርሃ ግብር በክልሉ የተሳካ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል።
የዲጂታላይዜሽን ክህሎት ዘመኑ የሚጠይቀውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማሳለጥ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በክልልም ሆነ በአገር ደረጃ የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ የዲጂታል ክህሎት የታጠቀ የሰው ሃይል ማፍራት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን በክልሉ ውጤታማ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።
ስለሆነም ለሶስት ዓመታት በሚቆየው የኮደርስ የስልጠና መርሃ ግብር ላይ በክልሉ 47 ሺህ 247 ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።
እቅዱን ለማሳካት ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የአመራር አካላት ወጣቱ የስልጠናው ተጠቃሚ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሯ አሳስበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን በበኩላቸው፤ ስልጠናው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በተለይም ወጣቱ በዚህ የኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስልጠና ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የዕድሉ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነር አቶ ፖል ገሪ ፤ ኢኒሼቲቩን ለማሳካት የተጠናከረ የቅስቀሳና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በማከናወን ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በኢኒሼቲቩ ማስጀመሪያ ሥነ ስርዓቱ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የአመራር አካላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር ሲሆን፤ በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና ለመውሰድ ያስችላቸዋል።
ስልጠናው በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰጥ ነው።