ኢትዮጵያን እንዴት ማገልገል እንዳለብን ተምረናል፤ የሉአላዊነቷ ዘብ ለመሆን ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን እንዴት ማገልገል እንዳለብን ተምረናል፤ የሉአላዊነቷ ዘብ ለመሆን ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው መማራቸውንና የሉአላዊነቷ ዘብ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ወንድማማቾቹ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ዳር ድንበርና የህዝቦቿ የመጨረሻ የሉዓላዊነት ምሽግ ነው።
ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር በሚል መርህ አንድያ ነፍሱን አስይዞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በጀግንነት ይጠብቃል።
ቅድሚያ ለእናት ሀገራችን ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችም የሀገራቸውን ጥሪ እየተቀበሉ መከላከያን መቀላቀል ባህል አድርገውታል።
የብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ40ኛ ጊዜ ካሰለጠናቸው መሰረታዊ ወታደሮች መካከል ሁለትም ሶስትም ወንድማማቾች በአንድ ጊዜ የተመረቁ ይገኙበታል።
ሶስቱ ወንድማማቾች መሰረታዊ ወታደር ሐይሉ ቱሲ፣ ሳሙኤል ቱሲና ዮሐንስ ቱሲ ከምሥራቅ ጉጂ ዞን ሻኪሶ ከተማ የመጡ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
ወንድማማቾቹ ከትውልድ ቀያችን ሺህ ኪሎ ሜትር አቋርጠን ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተገኘነው የኢትዮጵያ የሉአላዊነት ዘብ ለመሆን ነው ይላሉ።
በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤትም በቂ ስልጠና ማግኘታቸውንና ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ወንድማማቾቹ መሰረታዊ ወታደር ኦብሳ ዳሻ እና ነስሩ ዳሻ ውልደትና እድገታቸው ኢሊባቡር ሲሆን ሀገራቸውን በውትድርና ለማገልገል ተመካክረው መወሰናቸውን ይናገራሉ።
በወሰዱት ስልጠናና በገቡት ቃል መሰረት ለኢትዮጵያ እንደሚቆሙና ህይወታቸውን ሳይሰስቱ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ከአዲስ አበባ ራስጌ ከሱልልታ ከተማ ተነስተው የዘመቱት ደረጀ ለማና ፍቅሩ ለማ ለሀገራችን ሀለታችንም እናስፈልጋለን ብለው መከላከያን እንደተቀላቀሉ ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ዘብ በመሆን ዳርድንበሯንና ሰላሟን መጠበቅ ክብር መሆኑን በመጥቀስ ለዚህም ተዘጋጅተናል ብለዋል።