ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ለዘላቂ እድገት መረጋገጥ እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ፤ መስከረም 24/2017 (ኢዜአ)፦ የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትን ከኢንዱስትሪው ጋር በዘላቂነት በማስተሳሰር የአገርን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የኮንስትራክሽንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የኢንዱስትሪዎች የትስስር አገር አቀፍ ፎረም ዛሬ በድሬዳዋ ተመስርቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ዛሬ በድሬዳዋ በተካሄደው የፎረም ምስረታ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የኮንስትራክሽንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማት ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ ኃላፊ አቶ ተሾመ ዳንኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር ህጋዊ መዋቅር ተበጅቶለት ዘላቂ አገራዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።


 

በማሳያነት የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ቁጥር 1298/2015 መውጣቱን አስታውሰዋል።

ፎረሙ አዋጁን በተቀናጀ መንገድ ዕውን ለማድረግ የተመሠረተ መሆኑን አመልክተዋል።

የፎረሙ መመስረት ትስስሩን በማፅናት በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ሀይል ለማፍራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት እንዲሁም በምርምርና በጥናት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በጥራትና በፍጥነት በመፍጠር የአገር ከፍታና የብልጽግና ጉዞ ለማደላደል ያስችላል ብለዋል።

እንደ አቶ ተሾመ ገለፃ የፎረሙ መመስረት የትምህርት ዘርፉንና የኢንዱስትሪ ትስስርን ዘላቂና የጋራ ተጠቃሚነት ዕውን ያደርጋል።

በተለይ ኢንዱስትሪዎች ለመለዋወጫና ለቴክኖሎጂ ግኝቶች የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ፣ ተኪ ምርቶችን እንዲያመርቱና የተሻለ ተወዳዳሪ ሆነው የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ለማስቻል ወሳኝ ምዕራፍ ተጀምሯል ብለዋል።

በፎረሙ ምስረታ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ረሺድ በበኩላቸው በከፍተኛ ተቀማትና በኢንዱስትሪዎች መካከል የነበረው ያልተናበበና የተበጣጠሰን ጉዞ በማስቀረት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የፎረሙ መመስረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

እንደ አቶ አህመድ ማብራሪያ የፎረሙ ወደ ተግባር መሸጋገር የውጭ ቀጥታ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምርና ብቁና ተወዳዳሪ ምርቶችና የሰው ኃይል ለማፍራት መሰረታዊና ፈር ቀዳጅ ተግባር ነው።

የፎረሙ መመስረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪ ጥራት ያላቸው ምርቶች የማምረት እንዲሁም በክህሎትና በዕውቀት ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራት ሂደት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር የሚያግዝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ የዩኒቨርሲቲ ትብብርና የትምህርት ሽግግር ዳይሬክተር እሼቱ መኮንን(ዶ/ር) ናቸው።


 

የፎረሙ ዕውን መሆን ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣናና በአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በህግ የታሰረ ዘላቂ ትስስር በመፍጠር ለአገር ከፍታ የሚያግዙ ስራዎች ለመስራት ያስችለዋል ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም