ቀጥታ፡

ኢሬቻ የባህል አልባሳት ምርትና ግብይት እንዲነቃቃ ታላቅ ዕድል መፍጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ):-ኢሬቻ የአገር ባህል አልባሳት ከማስተዋወቅ ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው በቢሾፍቱ ከተማ የባህል አልባሳት ሻጮች ገለጹ። 

ኢሬቻ የአገር ባህል ልብሶች ምርትና ግብይት እንዲነቃቃ ታላቅ ዕድል መፍጠሩንም ነው ሻጮችና ሸማቾች የገለፁት። 

በኢሬቻ እና በሌሎች በዓላት የአገር ባህል ልብሶችን የመልበስ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡    

በባህል ልብስ ምርት እና ግብይት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ወይዘሮ ድንጊሊ ዳጩ እና ወጣት ሃይሉ ግርማ  ለዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የበርካታ አካባቢ መገለጫ የሆኑ የባህል ልብሶችን በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።  

ልብሶቹ ባህላዊ ትውፊቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው ጠቅሰዋል። 

በባህል አልባሳት ምርትና ንግድ ላይ የተሰማሩት በረከት ጸጋዬ እና ደሪቡ ገመቹ በበኩላቸው፤ ለበዓሉ የሚሆን የባህል አልባሳትን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከገበያ ባለፈ የባህል ልብሶችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ከጊዜ ወደ ጊዜ የባህል አልባሳት ግብይት መጨመሩን ተናግረዋል። 

የባህል ልብሶችን የመጠቀም ባህል ማደግ ለስራ እድል ፈጠራ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የገለጹት። 

የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ በነገው ዕለት በሆራ ፊንፊኔ የሚከበር ሲሆን ከነገ በስቲያ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ይከበራል።

ኢሬቻ የገዳ ስርዓት አንዱ መገለጫ ሲሆን የአንድነት፣ የወንድማማችነት እና የአብሮነት በዓል መሆኑም ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም