የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል እየተሰራ ነው
አዳማ ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ)፦የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን በሰንሰለቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
6ኛው ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ጉባኤ በአዳማ አባገዳ አደራሽ ተካሄዷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋለውን የመድኃኒት ብክነትና ምዝበራ ለመከላከል አገልግሎቱን ዲጂታል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በተለይ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎት ማሳለጥ፣ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ቆጠራና ኦዲት በዲጂታል መንገድ ለማከናውን እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
የዲጂታል አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ክፍተቶችን ለመሙላት ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
መድኃኒቶች በፍጥነት ወደ ተጠቃሚው መድረስ አለበት ያሉት ዶክተር መቅደስ፣ በተለይ የመድኃኒት ቅሸባና ብክነት ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ በጤና ተቋማት ዲጂታል የመድኃኒት አገልግሎት አሰጣጥ በስፋት ይተገበራል ብለዋል።
ዶክተር መቅደስ ከዚህ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት ማሳደግ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት ጥራትና ውጤታማነትን ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በመድሃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ላይ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከመቅረፉም ባለፈ የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው እንዳሉት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መርጃ መሳሪያዎች ተሰራጭተዋል።
በዚህም የወባ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መድኃኒቶችና ክትባቶች ለጤና ተቋማት መሰራጨታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም የስርጭት ሽፋኑን 69 በመቶ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
ለሀገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ትኩረት መሰጠቱን የገለፁት ዶክተር አብዱልቃድር በተለይ አምራቾችን የመደገፍና የማበረታታት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዲጂታላይዜሽን አንጻርም ''በ19ኝ የመድኃኒት ማከማቻና ማከፋፈያ ማዕከላትና ቅርንጫፎች የመረጃ አያያዝ ስርዓትን የማዘመን፣ የመጋዘን አያያዝ ዘመናዊነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተሻለ ክንውን ላስመዘገቡ ቅርንጫፎችና አጋር አካላት የገንዘብና ሌሎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።