የምስጋና ድምጾች ጎልተው የሚሰሙበት - ኢሬቻ

                                     

                                          የምስጋና ድምጾች ጎልተው የሚሰሙበት - ኢሬቻ

 

ኢሬቻ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ ኢሬቻ በሰውና በፈጣሪው እንዲሁም በሰውና በፍጥረታት መካከል ለሚኖረው የተፈጥሮ ህግ በአፋን ኦሮሞ “ሰፉ” ተገዢነቱን የሚገልፅበት ክብረ በዓል ነው፡፡ የተፈጥሮ ህግ እንዳይዛባ እስካሁን ላቆያቸው ፈጣሪ በጋራ ሆነው ለዋቃ ምስጋና የሚያቀርቡበት ነው፡፡ 

ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት ወይም ትስስር የሚያድስበት በዓል ነው፡፡ ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው፤ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት። ስለ ሰላምና አንድነት የሚዘመርበት፣ ስለመጪው ጊዜ መልካም ምኞት የሚገለጥበት፣ ሁሉን ላደረገ ፈጣሪ ምስጋና የሚቸርበት የአብሮነት በዓል ነው። በልመናው፣ በምርቃቱ፣ በምስጋናው ሁሉ ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን! አሜን! አሜን!) የሚሉ ድምፆች ይስተጋባሉ። የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ እሑድ መስከረም 26 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ ይከበራል።     

ኢሬቻ ለሁለት ትላልቅ ምክንያቶች የሚከበር ሲሆን ፈጣሪ ለሰው ልጅ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና ለማቅረብ ብሎም ወደ ፊት እንዲሆንለት ለሚፈልገው ነገር ፈጣሪን ለመማጸን ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከባዱን የክረምት ወራት በሙሉ ጤንነት ላሸጋገረው ዋቃ/ፈጣሪን መልካ በመውረድ ያመሰግናል፡፡ ሁሉን የፈጠረውን አምላክ፣ ሁሉን አሳልፎ ለዚያ ያበቃውን ፈጣሪ፣ በንፁህ ልቦና ወደ መልካ ወርዶ ያመሰግናል፡፡ ዓመቱም  የሠላም፣ የፍቅር፣ የስኬትና የብልጽግና እንዲሆንለትም ይለምናል፡፡ በዚህ ወቅት እርስ በርስም እንኳን ለቢራ /ፀደይ ወቅት/ አደረሳችሁ በመባባል ደስታውን ይገልጽበታል፡፡ 

ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን ኢሬቻ መልካ እና ኢሬቻ ቱሉ በመባልም ይታወቃሉ፡፡ ኢሬቻ መልካ በወርኃ መስከረም በመልካ/በውኃ ዳርቻ ላይ የሚከበር በዓል ነው፡፡ ኢሬቻ መልካ የሚከበረው በመስከረም ወር ከመስቀል በዓል በኋላ ሲሆን፤ የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው። 

የኦሮሞ ህዝብ በክረምት ወራት ዝናብ ለሰጠውና በሰላም ወደ ጸደይ ላሸጋገረው ዋቃ/ፈጣሪ ምስጋና ያቀርባል፡፡ በቀጣይም ቡቃያው ከየትኛውም የተፈጥሮ አደጋ ተጠብቆ፤ በሰላም ወደ ጎተራው እንዲገባ ፈጣሪን የሚማጸንበት ነው፡፡  

ሁለተኛው ኢሬቻ ቱሉ ሲሆን ይህም የሚከናወነው የበጋው ወራት ተገባዶ የበልግ / የአርፋሳ ወቅት ሲገባ ነው፡፡ በአቅራቢያ በሚገኙ ተራራማ ቦታዎች ላይ በመውጣት ለመጪው ክረምት ዝናብ ስጠን፣ ወራቱን የአዝመራ ጊዜ አድርግልን፣ በማለት ፈጣሪን ይለምናሉ፡፡ 

''እርጥበት አትንፈገን፣ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡ፤ የዝናብ ንፋስ ስጠን'' በማለት ለፈጣሪ ተማጽኖ የሚቀርብበት ነው። "ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሰላም አድርግልን፣ የሰላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን" እያለ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡ 

በኢሬቻ በዓል የፈጣሪ ምህረት፣ ዕርቅ፣ እዝነት እና በዓሉ የሰላም በዓል እንዲሆን ኦሮሞ ፈጣሪውን ይጠይቃል፤ ይማፀናል፤ ለተደረገለትም ነገር ሁሉ ያመሰግናል። የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት መገለጫ ሲሆን፤ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር የቆየ በዓል ነው።   

ኢሬቻ አብሮነትን በማጠናከር ፈጣሪያቸውን ለማመስገን የወጡ ሰዎች በንፁህ ልቦና ፈጣሪያቸውን አመስግነው ተደስተው የሚመለሱበት፣ አንድነታቸውንና ወንድማማችነታቸውን የሚያጠናክሩበት ነው። በኢሬቻ ከተለያየ ስፍራ የሚመጡ ተሳታፊዎች ያለምንም ልዩነት፣ በፍቅርና በአንድነት ፈጣሪን ያመሰግናሉ፡፡ ኢሬቻ የኦሮሞን አንድነትና የብሔር ብሔረሰቦች ወንድማማችነት ከማጠናከር አንፃር ምቹ መድረክ ነው፡፡

ኢሬቻ ከመድረሱ በፊት አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች በየአከባቢው እየሄዱ በማህበረሰቡ መካከል ቅሬታና አለመግባባት ካለ እንዲፈታ፣ ይቅር እንዲባባሉ፣ ደም የተቃባ ካለ ጉማ /ካሳ/ እንዲከፍል ያደርጋሉ፡፡ ይህም እርቅ ሳያወርዱ ቂም ይዞ ለምስጋና ወደ ኢሬቻ መሄድ የተከለከለ ስለሆነ ነው፡፡ 

ኢሬቻ በንፁህ ልቦናና በንፁህ አእምሮ፣ ያለ ቂምና ቁርሾ ተኬዶ ሠላም የሚሰበክበት፣ ለምስጋና መልካ ከተወረደ በኃላም አባገዳዎች እርስ በርሳችሁ ይቅር ተባብላችኃል? እርስ በርሳችሁ ሠላም ናችሁ? ከፍጥረታትና ከፈጣሪ ጋር ሠላም አውርዳችኃል? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ምናልባት በየአከባቢው እርቅ ሳያወርድ የመጣ ካለ እንኳን በዚህ ወቅት ይቅርታ በመጠያየቅ ምስጋናውን አቅርቦ ይሄዳል፡፡ 

ለምስጋና እርጥብ ሳር ይዞ የሚወጣ ሰው ቂምና ጥላቻን አስወግዶ፣ ሠላምን፣ ወንድማማችነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ተስፋን፣ ብልፅግናንና መልካም ምኞትን ይሰብካል፤ ያውጃል፡፡ ከፈጣሪው ለተሰጠው ስጦታ እውቅና ይሰጣል፤ ያመሰግናል፡፡ በፍጥረታትና በፈጣሪ መካከል ያለውን ትስስር ያደንቃል፡፡ 

ሲያመሰግንም ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት፣ ለአጠቃላይ ለሰው ልጅ፣ ለሀገር ሠላምና ፍቅር በመመኘት ይዘምራል፤ ያመሰግናል፤ ይለምናል፡፡ ይህ ደግሞ ኢሬቻ የእርቅና የሠላም ተምሳሌት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኢሬቻ የሠላምና የእርቅ መድረክ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ነው ኦሮሞ ሰው እርስ በርሱ ከታረቀ ፈጣሪም ይታረቀዋል ብሎ የሚያምነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢሬቻ ምርቃት የሚሰጥበትና የሚቀበሉበት ስፍራም ነው፡፡ 

ኢሬቻ እሴቶች የሚጎሉበት መድረክም ነው። ለአብነትም በዘመናዊ መንገድ በተዘጋጁ የባህል አልባሳት ደምቆ መታየት የኢሬቻ መልክ ነው። በዚህም ለባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ አምራቾች ገበያ እንዲሁም ለበርካቶች የስራ ዕድል በመፍጠር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በተጨማሪም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም