በክልሉ የለማው ሰብል የሚጠበቀውን ምርት መሰብሰብ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የለማው ሰብል የሚጠበቀውን ምርት መሰብሰብ የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል
ደሴ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በመኸር ወቅቱ ከለማው ሰብል ቁመና የታቀደውን ምርት መሰብሰብ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የማሽላ ሰብል ጉብኝት ተካሄዷል።
በጉብኝቱ ወቅት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ገጠር ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ ለመኸር ወቅት በታቀደው መሰረት 5 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ለምቷል።
ከለማው መሬት 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
እቅዱን ማሳካት የሚያስችል የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የተባይና አረም ቁጥጥር ሥራ በቅንጅት መከናወኑን ጠቁመው፤ ምርቱ ወደ ጎተራ እስከሚገባ ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የዘንድሮው የዝናብ ስርጭትና የግብዓት አቅርቦት ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ እንዳስቻለው አመልክተዋል።
''ዛሬ በአርጎባ ወረዳ የተመለከትነው የሰብል ቁመናም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ ነው'' ያሉት ኃላፊው፤ ይህም ባለፈው ዓመት በተወሰኑ አካባቢዎች በተከሰተው የዝናብ እጥረት የገጠመውን የምርት መቀነስ በማካካስ በምግብ ራስን ለመቻል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደሆነ አብራርተዋል።
ፈጥኖ የሚደርሰውን ሰብል ከብክነትና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ በመከላከል በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመሰብሰብ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም ካለው የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ኮምባይነር በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች ጭምር በኪራይ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በበኩላቸው፤ በዞኑ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት ለመላቀቅ በቂ ግብዓት ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የዘንድሮው የመኸር ሰብል ልማት የተሻለ ምርት መስጠት የጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በወቅቱ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዲገባ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
''በመኸር ወቅቱ ከለማው 432 ሺህ ሄክታር መሬት 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ናቸው።
ባለፈው ዓመት በተለያዩ ወረዳዎች ባጋጠመው የተፈጥሮ ችግር ከፍተኛ የምርት መቀነስ አጋጥሞ እንደነበረ አስታውሰው፤ የዘንድሮው የሰብል ቁመና ያለፈውን የሚያካካስ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም እንድሪስ እንደገለጹት፤ በልዩ ወረዳው ባለፈው ዓመት ባጋጠመ የዝናብ እጥረት የተስተዋለውን የምርት መቀነስ ማካካስ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው።
በዚህም በመኸር ወቅት በተለያየ የሰብል ዘር ከለማው 7 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ከ187 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በጉብኝቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራር አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።