የተለያዩ መጻሕፍትን በማቅረብ የትውልዱን የንባብ ባህል ለማጎልበት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ መጻሕፍትን በማቅረብ የትውልዱን የንባብ ባህል ለማጎልበት እየተሰራ ነው

ዲላ፤ መስከረም 24/2017 (ኢዜአ)፦የተለያየ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን በማቅረብ የትውልዱን የንባብ ባህል ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ ከጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "የንባብ ባህል ለትምህር ጥራት" በሚል መሪ ቃል የንባብ ሳምንት በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ እያካሄደ ነው።
በከተማው እየተካሄደ ያለው የንባብ ሳምንት የመጻሕፍት አውደርዕይ፣ የፓናል ውይይት እና የህፃናት ንባብን ያካተተ መሆኑም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባተ ካሰው በወቅቱ እንደገለጹት፣የንባብ ሣምንት መከበሩ የዜጎችን የንባብ ባህል በማጎልበት የሚያነብ ትውልድ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።
አገልግሎቱ ዜጎች በተለይ ታዳጊ ተማሪዎች የንባብ ባህላቸው እንዲጎለብት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ለዚህም የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት በማቅረብ ትውልዱ እውቀትና ሃሳብ እንዲገበይ እየተደረገ ነው" ብለዋል።
በዲላ ከተማ የንባብ ሣምንት ሲዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፣ ይህም የአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ መጻሕፍት የሚያገኝበትን አማራጭ የሚያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።
በሣምንቱ የንባብ ባህልን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ ያሉት ሃላፊው፣ በተለይም ከ3 ሺህ 800 በላይ መጻሕፍት ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለህዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ ለማረሚያ ቤቶችና መሰል ተቋማት በነጻ እንደሚሰራጩ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በንባብ ሳምንቱ ከሚካሄደው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ በተጨማሪ፣ የንባብ ክበባትን የማቋቋምና የመደገፍ እንዲሁም የስነ ጽሁፍ ምሽቶች እንደሚካሄዱ አቶ አባተ አስረድተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ የንባብ ክህሎት እንዲዳብር ትኩረት ስጥቶ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኤልያስ አለሙ ናቸው።
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ንባብ ሞጋች፣ አካባቢውን የሚገነዘብና ለለውጥ የሚተጋ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
የአካባቢው ማህብረሰብ የንባብ ሣምንት ያሉትም ጥቅሞች በአግባቡ ተረድቶ ለውጤት እንዲተጋም ነው ያሳሰቡት
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በበኩላቸው ንባብ ትውልዱን በመልካም ባህርያት ከማነጽ ባለፈ የጽሁፍ ክህሎቱና አዳዲስ እውቀቶችን እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ በተለይ በወጣቱ ክፍል ያለው የንባብ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህንን ለመቀየር የሁሉም አስተዋጾ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ በተለይ ወጣቱ የንባብ ጥቅምን በአግባቡ ተረድቶ የንባብ ክህሎቱን እንዲያዳብር ቤተ መጻሕፍትን በማደራጀት አማራጮችን ለማስፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ምሁራን፣ ደራሲያን፣ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ የንባብ ሣምንት በመጪው እሁድ በይርጋጨፌ ከተማም እንደሚካሄድም ታውቋል።
-