የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከ150 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የግብርና ልማት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከ150 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የግብርና ልማት እያከናወነ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከ150 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የግብርና ልማት እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ከትምህርት፣ ከምርምርና ከማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተልዕኮው በተጓዳኝ በምግብ ራስን የመቻል ራዕይ አንግቦ በሁለት ሳይቶች ላይ ከ150 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እያለማ መሆኑን ገልጿል።
በዚህም እርሻ፣ እንስሳት እርባታ፣ ንብ ማነብ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ስራዎች መሆናቸውን የገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ ልማትና ቢዝነስ ምክትል ኮማንዳንት የውስጥ ገቢ ዳይሬክተር ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል መስፍን ስዩም ናቸዉ፡፡
በዚህም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ካሮት፣ ድንች፣ ሰላጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ እና ማንጎ የመሳሰሉ የግብርና ውጤቶችን በስፋት እያለማ እንደሚገኝም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
የተቋሙን በምግብ ራስን የመቻል አቅጣጫ እውን በሚያደርግ መልኩ ዩኒቨርሲቲው በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን መቄት ወረዳ እና አካባቢው ላይ ከ120 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ውጤታማ የስንዴ ሰብል እያለማ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በግቢው ውስጥም 30 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ላይ እንደሚገኝም ሌተናል ኮሎኔሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከሚያከናውነው የግብርና ልማት ስራ ባሻገር የማህበረሰቡን ጠንካራ የተቀናጀ የልማት ተነሳሽነት በመፍጠር በኩል ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በምስራቅ ሽዋ ዞን ቦቴ አካባቢ ለሚገኝ ትምህርት ቤት 7 ሄክታር መሬት በእራሱ ወጪ አርሶና ዘርቶ በማስረከብ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በግቢው ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም በአመት ከሁለት እና ሶስት ጊዜ በላይ የተለያዩ አትክልቶችን በማልማት ለተማሪዎችና ለግቢው ማህበረሰብ በቅናሽ ዋጋ እያቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡