ቀጥታ፡

"ልጅ እያላችሁ እናታችሁን አገልግሉ ስታድጉ ለአገራችሁ ዘብ ሁኑ" የሚለውን የአባታቸውን ምክር ተቀብለው ለኢትዮጵያ ዘብ የቆሙት ሶስቱ ወንድማማቾች

ጋሻው ሲሳይ፣ ዘመድኩን ሲሳይና ዘላለም ሲሳይ ይባላሉ፤ ትውልድና ዕድገታቸው አርሲ አሰላ ነው።

ወንድማማቾቹ የወታደር ልጆች ወጥቶ አደሮች ናቸው፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለመጠበቅ የቆረጡ ጀግኖች።

አባታቸው የቀድሞ ሰራዊት አባል በመሆን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ዘብና አለኝታ ሆነው አገልግለዋል።

የአባታቸውን ታሪክ እና ገድል እንዲሁም ስለሀገር ፍቅር እየሰሙ ያደጉት ልጆቻቸውም መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል በብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተመርቀዋል።

አባታቸው ገና ከልጅነት ጀምሮ "ልጅ እያላችሁ እናታችሁን አገልግሉ ስታድጉ ለአገራችሁ ዘብ ሁኑ" በሚል ምክር የእናትና የሀገርን ተምሳሌታዊ ቁርኝት እያስረዱ እንዳሳደጓቸው ይናገራሉ።

የዘመድኩንና የዘላለም ታላቅ የሆነው ጋሻው ሲሳይ ለሀገር ዘብ መቆምን ከአባቴ ተምሬ በመወሰኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ ይላል።

የአገር ምልክት የሆነውን የክብር ልብስ ለብሶ ኢትዮጵያን ከመጠበቅ የበለጠ የሚያኮራ ነገር እንደሌለም ይናገራል።

የእርሱ ተከታይ ዘመድኩን ሲሳይ፤ የአባታቸውን ገድል ለማስቀጠል መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀሉን ገልጿል።

ዘላለም ሲሳይ በበኩሉ፤ ለሀገር ክብር መቆም እንደሚያስከብር በመጥቀስ ለኢትዮጵያ በውትድርና መስክ መሰለፍ የልጅነት ህልሙ እንደነበር አስታውሷል።  

ሶስቱ ወንድማማቾች የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸውና የሀገራቸውን ዳር ድንበር እንዲያስከብሩ መርቀው ለሸኟቸው አባታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ስልጠናውን በብቃትና ሙያዊ ስነምግባርን በተላበሰ አግባብ ማጠናቀቃቸውን ገልፀው፤ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ግዳጅ ሁሉ በብቃትና በሀላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን አክብሮ ከማስከበር በላይ ጀግንነት ባለመኖሩ ወጣቶች መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም