በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የተሳካና ግብዓቶች የተገኘበት ነው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የተሳካና ግብዓቶች የተገኘበት ነው - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ሠመራ፤ መስከረም 23/2017(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የተሳካና ግብአቶች የተገኘበት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ከክልሉ 49 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከመስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሄዱ የቆዩት አጀንዳ የመለየት የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ(ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተወከሉ ወኪሎች አጀንዳዎቻቸውን ለይተዋል።
የምክክሩ ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን በአደራ ተረክበው በቀጣይ ቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚወያዩ ወኪሎቻቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመምረጥ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የተመረጡት ወኪሎቻቸው በቀጣይ ባሉት ሶስት ቀናት በባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የሚሳተፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አጀንዳ የማሰባሰቡ የምክክር ሂደቱ የተሳካና ግብዓቶች የተገኘበት መሆኑንም ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
ለሂደቱ መሳካት የክልሉ መንግስትና ሌሎች አካላት ላደረጉት ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን በበኩላቸው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከቅዳሜ ጀምሮ ውይይት ይካሄዳል ብለዋል።
በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማህበራት፣ የመንግስት አካላትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚሳተፉበት መሆኑን አመልክተው፤ ገንቢ ሃሳቦችን በማደራጀት እንዲሳተፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በክልሉ የምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ከ800 በላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ወኪሎች መሳተፋቸው ተመልክቷል።