ኢዜአ ነባሩን ህንፃ በማሳደስ ለሥራ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ሥምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ነባሩን ህንፃ በማሳደስ ለሥራ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ሥምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነባሩን ህንፃ በማሳደስ ለሥራ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ሥምምነት ተፈራረመ።
የእድሳት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ጋር ተፈራርመዋል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል፤ ሁለቱም ተቋማት ለሀገር ትልቅ ሥራ የሰሩ እና በመሥራትም ላይ ያሉ የሀገር ባለውለታዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከለውጡ በኋላ ባለፉት ስድስት ዓመታት ተቋማቱ ይበልጥ ተቀራርበው በመደጋገፍ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የዚህን ታላቅ ተቋም ሥራዎች በማገዝ ለላቀ አገልግሎት ድጋፍ ማድረግ ተገቢና የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም መሠረት ለረዥም ዓመታት ያገለገለውን የተቋሙን ነባር ህንፃ በማደስ ምቹና ማራኪ ለማድረግ ስምምነት ተፈራርመናል ብለዋል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በዘመናዊ አሠራር በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢዜአን ህንፃ በጥራትና በፍጥነት ምቹና ዘመናዊ ሆኖ በተያዘለት ጊዜ እድሳት የሚደረግለት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ሁለቱ ተቋማት በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
የቤቶች ኮርፖሬሽን ኢዜአ በሚሰራቸው ሥራዎች ውስጥ ትልቅ እገዛ እና ድጋፍ እያደረገ ይገኛልም ብለዋል።
በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዘመናዊ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢዜአን ነባር ህንፃ ማደስ ለተቋሙ የሚዲያ ስራዎች የላቀ ስኬት አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል።
ኮርፖሬሽኑ የእድሳት ሥራውን በጥራትና በፍጥነት እንደሚያከናውን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።
በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ነው።