ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፓኪስታን ገበያ የምታቀርበውን የወጪ ምርት ለማሳደግ እንደምትፈልግ ገለፀች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በፓኪስታን ገበያ የምታቀርበውን የወጪ ምርት ለማሳደግ እንደምትፈልግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያንን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡


 

በውይይቱ ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ፓኪስታን የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፓኪስታን ገበያ የምታቀርበውን የወጪ ምርት በመጠን፣ በጥራትና በአይነት በማሳደግ አሁን ያለውን የንግድ ሚዛን ማጥበብ እንደምትፈልግ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱንና የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች በፓኪስታን ገበያ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

አምባሳደሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እና ብዙ ህዝብ ያላት በመሆኗ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንደምትፈልግ ማንሳታቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም