ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችል የየብስና የባቡር ትራንስፖርት ሪፎርም እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን ማድረግ የሚያስችል የየብስና የባቡር ትራንስፖርት ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የባቡርና የየብስ ትራንስፖርት ሪፎርም በተመለከተ አውደ-ጥናት አካሂዷል፡፡


 

አውደ ጥናቱ የዘርፉ ችግሮች ከአስተዳደር፣ ከአገልግሎት፣ ከፖሊሲና መሠረተ-ልማት ማሟላት አንፃር እንዴት ይፈቱ? የሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተነስቷል።

የባቡር መለዋወጫ እቃዎች እጥረት፣ መስመሮች ባቡሮችን በሚፈለገው ፍጥነት ማስተናገድ አለመቻል፣ የተቀናጀ የፖሊሲ አቅጣጫ ውስንነት፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ የፋይናንስ እጥረት በሪፎርሙ ፈታኝ ከሆኑት ችግሮች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፤ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የእድገትና ብልጽግና ጉዞ ስኬት የሎጂስቲክስ ዘርፉ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሀገር በሚመዘገበው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልክ የሎጂስቲክስ አፈጻጸሙ ውጤታማ ካልሆነ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣትም አዳጋች መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ16 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የተሻገረው የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ በቅርብ ዓመታት በሁለት እጥፍ እንደሚያድግ ጠቁመው፤ ለዚህ የሚመጥን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ የገቢና ወጪ ጭነት 85 በመቶ የሚሆነው በተሽከርካሪ እንደሚጓጓዝ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህን አዎንታዊ እድገቶች ለማስቀጠል በባቡርና በየብስ ትራንስፖርት ላይ መሠረታዊ ለውጥ/ሪፎርም/ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ 95 በመቶ በጅቡቲ ወደብ በኩል እንደሚጓጓዝ ገልጸው፤ ካለን ግዙፍ ኢኮኖሚ አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር መስመር ሲሰራ በዓመት 10 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማጓጓዝ ይችል የነበረው አሁን ከ2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደማይሻገር ገልፀዋል፡፡

በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንዲችል ተደርጎ ቢሰራም በአርብቶ አደሮችና እንስሳት በሚበዙበት አካባቢ ስለሚያልፍና በሌሎች ችግሮች በሰዓት ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ እንዳይጓዝ አድርጎታል ብለዋል።

በመሆኑም ሪፎርሙ በባቡር መሠረተ-ልማት፣ በአገልግሎት፣ በፋይናንስና ሌሎችም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አስፈልጓል ሲሉ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ተቀርፆ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው፤ የባቡርና የየብስ ትራንስፖርት መስመሮችን ከደረቅ ወደቦች ጋር ማስተሳሰር የቀጣይ ትኩረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሪፎርሙ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ዘርፉ ለጥቅል የኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ማሳደግ ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የዓለም ባንክ የሞጆ ደረቅ ወደብን የሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ የሚሠራውን ማስፋፊያ ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም