በጎንደር ከተማ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለፍጻሜ ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ ነው
ጎንደር፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ከፍጻሜ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት አራተኛ ዙር 12ኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ቻላቸው ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት፤ በከተማው በፌዴራል መንግስት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡
በከተማው የተጀመሩት የኮሪደር ልማትና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥገና ስራዎች የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር የከተማውን የቱሪዝም ገቢ ማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ግንባታቸው ተጓቶ የቆየው የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ስራና የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት ዳግም ስራቸው በፍጥነት መጀመሩን አስታውሰው፤ የህዝቡን የልማት ጥያቄ በመፍታት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡
የጸጥታ መዋቅሩን መልሶ በማደራጀት የከተማውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ 23 የሚሊሻና የፖሊስ አባላትም ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የከተማውን ሰላም በማወክ የወጣቱን መልካም ሰብዕና በሚጎዱ ተግባራት ላይ የተሰማሩ 160 ቁማር ቤቶችና 162 ጫት ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የከተማውን ህዝብ ስጋት ላይ ጥሎት የቆየውን የሰው እገታ ወንጀል ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችንም ለህግ ለማቅረብ በተደረገው ርብርብ 19 ተጠርጣሪዎችን በህግ ጥላ ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ተግባራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑም ህብረተሰቡ ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
''በከተማው የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚፈቱ ናቸው'' ያሉት የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሪት እናትነሽ ዋለ ናቸው፡፡
አስፈጻሚ አካሉ በሰላም ፣በልማትና በመልካም አስተዳደር ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በአዲሱ የበጀት ዓመትም በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ተግባራትን ቆጥሮ መፈጸም እንደሚገባ አመልክተዋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ተረፈ ሁነኛው በበኩላቸው፤ ህዝብን ለምሬት የዳረጉ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ጨምሮ ሙስናና ሌብነት በመከላከል ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በከተማው የሚስተዋሉ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታን በመቆጣጠር ከተማ አስተዳደሩ በሃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ተግባሩን ሊያከናውን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ዘመነ መወሻ፤ የሰው እገታ ወንጀል የከተማውን መልካም ስምና ገጽታ ያጎደፈ ድርጊት በመሆኑ ድርጊቱን በመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የምክር ቤቱ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።