ቀጥታ፡

የአፍሪካ ጠበቆች ማህበራት ሕብረት ጉባኤ ከጥቅምት ስድስት እስከ ጥቅምት ዘጠኝ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):- አስራ አራተኛው የአፍሪካ ጠበቆች ማህበራት ሕብረት ጉባኤ ከጥቅምት ስድስት እስከ ጥቅምት ዘጠኝ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር አስታወቀ፡፡

በጉባኤው በአፍሪካ የሚገኙ የጠበቆች ማህበራት ፣ አህጉራዊ ድርጅቶች ፣ዓለም አቀፍ የጥብቅና ድርጅቶች የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ ተወካዮችን ጨምሮ ከ300 በላይ የአገራት ተወካዮች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የአፍሪካ ጠበቆች ማህበራት ህብረት 55ቱን የአፍሪካ አገራት የጠበቆች ማኀበራት ስምንት አካባቢያዊ ተቋማትን ጨምሮ 1 ሺህ 2ዐዐ የሚደርሱ መደበኛና ልዩ ኢንዳውመንት አባላቶችን የያዘ የአህጉሪቱ መሪ የሕግ ተቋም ነው፡፡ 

በዚህም አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና መሰል ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በርካታ የስራ ግንኙነትን እያከናወነ እንደሚገኝ የአለም አቀፍ አዘጋጅ ኮሚቴው አስተባባሪና የአፍሪካ ጠበቆች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ 

አስራ አራተኛውን የተቋሙን ጠቅላላ ጉባዔ እንድታዘጋጅ ተመርጣ የነበረችው የሞሮኮዋ ማራካሽ ከተማ እንደነበረች አቶ ቴዎድሮስ በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን የማህበሩ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ፌብሩዋሪ 2024 በካሜሮን ያውንዴ ከተማ ባደረገው ስብሰባ የአዘጋጅነት እድሉ ከሞሮኮ ተነጥቆ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅሰዋል፡፡ 

በዚሁ መሠረት አስራ አራተኛው የአፍሪካ ጠበቆች ማኀበራት ሕብረት ጉባዔ ከጥቅምት ስድስት እስከ ጥቅምት ዘጠኝ ቀን 2017 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

በመድረኩ ኢትዮጵያውያን ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች እንዲሁም አጋር አካላት የነቃ ተሳተፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡  

ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን የሕግ ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ሂደት የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል። 

ማህበሩ ከ 22 አመት በፊት በአዲስ አበባ መመስረቱ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም