ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ የዲጂታል ሥርዓትን በይፋ ሥራ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ የዲጂታል ሥርዓትን በይፋ ሥራ አስጀመሩ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ መቀበያ የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን (NCRS) ሥራ አስጀመሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስጀመሪያ መርሐግብሩ ላይ እንዳሉት፤ መንግሥት የተቋማትን አሠራር ለማዘመን፣ ተጠያቂነትና ግልፅነትን ለማሻሻል እየሠራ ነው።
በዛሬው እለት በይፋ ሥራ የጀመረው ብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ ሥርዓትም የተቋማትን የመፈጸም አቅም የማሳደግ የሪፎርም አካል ነው ብለዋል።
የሙስና ወንጀል የብልሹ አስተሳሰብ ባህልና አሰራር ውጤት በመሆኑ በሪፎርሙ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሙስና ወንጀል እንጂ ጊዜያዊ ሀብት በማጋበስ የሚገኝ ክብር እንዳልሆነ በመገንዘብ ድርጊቱን የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት የጋራ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ዜጎች ያላቸውን ሚና የሚያሳድግ፣ የተቋማት ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግ የላቀ ሚና እንዳለው አንስተው ተቋማት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ተቋማት የማስተባበርና የመከታተል ሚናቸውን ሊያጠናክሩም ይገባል ነው ያሉት።
የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የለማው የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ መቀበያ የዲጂታል አሠራር ሥርዓትን (NCRS)
ጥቆማዎች ሚስጥራዊነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል።
የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፤ በለውጡ ዓመታት ጠንካራና ገለልተኛ ተቋም ለመገንባት በርካታ ሥራዎች መተግበራቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ ሀገራዊ የፀረ ሙስና ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የዲጂታል ሥርዓትን መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ለአብነትም የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ አሠራርን ወደ ዲጂታል ሥርዓት መግባቱን ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የሆነው ብሔራዊ የሙስና ወንጀል ጥቆማ የዲጂታል ስርዓትም የዜጎችን የመረጃ ሰጪነትና ተሳትፎ ለማሳደግ፣ የሙስና መከላከል ሥራን ውጤታማ ለማድረግና የመልካም አስተዳደር ሥራን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በዚህም ተቋማት በመረጃ ላይ የተመሠረተና እውቀት መር አመራርና ውሳኔ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን የሚያሻሽሉ ሥርዓቶችን እየዘረጋ ነው ብለዋል።
ሙስና በረቀቀ መንገድ የሚፈጸም ወንጀል በመሆኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን መተግበር ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት አራት ወራት ብሔራዊ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ሥርዓትን አልምቶ ለኮሚሽኑ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ፤ የዲጂታል ስርዓቱ (NCRS) የሙስና ጥቆማ ለመቀበል የሚያስችል፣ የጥቆማ ሰነዶችን ለምርመራ ለማደራጀት፣ የተደራጁ መረጃዎችን ለሚመለከታቸው ተቋማት ለማጋራት፣ 25 ዓይነት የሙስና ዓይነቶችን በመለየት ጥቆማዎችን መቀበል የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
ዲጂታል ስርዓቱ ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ የቴክኖሎጂ አሰራር ስርአት እንደሆነም ተነስቷል።
የNCRS መተግበሪያን ስልክ ላይ በመጫን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛ ወይም በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ጥቆማ መስጠት ይቻላል ተብሏል።