የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያሳድጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያሳድጉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ አመራሮች ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ኮንሰርቲየም ሰብሳቢ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ በተሻለ መልኩ ስለሚሳተፉበት ሁኔታና ስለሚኖራቸው ሚና ሀሳቦች ተነስተው መግባባት ተደርሶባቸዋል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ጉዳዮች መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ነው።
የዛሬ ውይይት ቀደም ሲል የተደረገውን ስምምነት መሰረት ያደረገ መሆኑን ኢዜአ ከኮሚሽኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።