የስፖርት ልማትን በማጠናከር ዘርፉ ለአገር እድገት እና ልማት ያለውን ድርሻ ማሳደግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ልማትን በማጠናከር ዘርፉ ለአገር እድገት እና ልማት ያለውን ድርሻ ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):- የስፖርት ልማት ስራን ይበልጥ በማጎልበት ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘትን የሚገባትን ጥቅሞች ማሳደግ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በስፖርት ፖሊሲና ረቂቅ አዋጅ ላይ ከስፖርት ባለሙያዎች ጋር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ውይይት እያደረገ ነው።
ባለሙያዎቹ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት የተወጣጡ ናቸው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ስፖርቱን በተደራጀ መንገድ ለመምራት የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ስፖርት ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ የዘርፉን ልማቱን በማፋጠን ሀገር ማግኘት የሚገባትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ጤናማ ዜጋ እና በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረኮች ተወዳዳሪና አሸናፊ የሆኑ ስፖርተኞችን በማፍራት ስፖርት ለሀገር ብልጽግና ያለውን ሚና ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ከዚህም አንጻር የስፖርት ባለሙያዎች ለሕግ ማዕቀፎቹ ተገቢ ግብአት በመስጠት ስፖርቱ እንዲያድግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ረቂቅ የስፖርት ፖሊሲውን አስመልክቶ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።
በውይይቱ የስፖርት ፖሊሲውን አስመልክቶ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።