አገራዊ ምክክሩ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው-በሠመራ የውይይቱ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው-በሠመራ የውይይቱ ተሳታፊዎች
ሠመራ፤መስከረም 23/2017 (ኢዜአ)፦አገራዊ ምክክሩ አንድነታችንን የምናጠናክርበት የትብብር ጉዞን የሚያመቻች ነው ሲሉ በሠመራ እየተካሄደ ባለው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ የወጣት ተወካዮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በማካሄድ ላይ ነው።
እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የወጣቶች ተወካዮች በሂደቱ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ውይይት እያደረግንበት ነው ብለዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል የሠመራ ከተማ ወጣት ተወካይ ወጣት መዓድ ዓሊ፥ የምክክር ሂደቱ አሁን የደረሰበት ምዕራፍ "እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ቀደምት አባቶቻችን በአንድ ላይ እንድንቆም መንገድ የሚያሳየን ነው" ብሏል።
ለአገር ዕድገት የምንተባበር እና የምንፀና ከሆነ በቀጣይነትም የአገራችን ለውጥ ላይ ቁጭ ብለን እንድንመካከር የጋበዘ መድረክ መሆኑን ተረድተናል ብሏል።
ከኮነባ ወረዳ የመጣው የወጣቶች ተወካይ መሐመድ ኡትባን በበኩሉ መስማማት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ እንድናተኩር የምክክር ሂደቱ እድል መፍጠሩን ጠቁሟል።
ከአይሳኢታ ወረዳ ወጣቶችን ወክሎ የመጣው አሊሚራህ የሱፍ እንዳለውም ቀደምት አባቶች አንድነታቸውን አጉልተውና ልዩነታቸውን አጥብበው ኢትዮጵያን እዚህ ማድረሳቸውን አስታውሷል።
አባቶቻችን የብሄር፣ የሐይማኖትና የቀለም ልዩነት ሳይገድባቸው ችግሮችን ማለፍ መቻላቸውን አስረድቷል።
የምክክር መድረኩ እንድንወያይ ያደረገን በመሆኑ ችግሮቻችንን እንድንፈታ የሚያግዝ ነው ያለችው ደግሞ የተላላክ ወረዳ ወጣት ተወካይ አሚና ሙሳ ነች።
በመሆኑም በሠላም፣በፍቅርና በአንድነት መጓዝ እንድንችል ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ መልካም ግብዓት የሚገኝበት ነው ብላለች።
በሰመራ እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የየማህበረሰቡ ተወካዮች የቡድን ውይይታቸው እንደቀጠለ ነው።