14ኛዉ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
14ኛዉ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም 23/2017(ኢዜአ)፦14ኛዉ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ጉባኤ ከጥቅምት 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።
የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው ጉባኤውን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንደሚካሄድና በዘርፉ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።
ጉባኤውን የተሳካ ለማድረግ 17 አስተባባሪ አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።
በመላው አፍሪካ አገራት የሚገኙ የጠበቆች ማኅበራት መሪዎች ዓለም አቀፍ የጥብቅና ድርጅቶች የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ተወካዮች ከ300 በላይ የተለያዩ አገራት ተወካዮች በጉባኤው እንደሚታደሙ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲው የተለያዩ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች ኃላፊዎችና ተወካዮች ጨምሮ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር አባላትም በጉባኤው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን የሕግ ሥርዓቱን ለማዘመን በሚደረገዉ ሂደት ውስጥ የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበራት ኅብረት ከ22 ዓመታት በፊት 54ቱን የአፍሪካ አገራት የጠበቆች ማኀበራት፣ ስምንት አካባቢያዊ ተቋማትን እንዲሁም 1 ሺህ 100 በላይ አባላቶችን የያዘ የአህጉሪቱ መሪ የሕግ ተቋም ነው።