ኢትዮጵያ የባቡርና የየብስ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚያሳልጥ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እያደረገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባቡርና የየብስ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚያሳልጥ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እያደረገች ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባቡርና የየብስ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚያሳልጥ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እያደረገች መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የባቡርና የየብስ ትራንስፖርት ሪፎርም እያካሄደ ሲሆን ይህንን በተመለከተ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተዘጋጅቷል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የባቡር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ሁነኛ መሳሪያ ነው።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ከሚፈለገው አንፃር በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዘርፉ የአገሪቱን ብልፅግና የሚያረጋግጥ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የካርጎ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ 99 በመቶ የሚሆነው በባቡርና በየብስ ተሽከርካሪ የሚጓጓዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያ ዘርፉ ዋና የትኩረት ማዕከል እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት አዋጅን ጨምሮ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ገቢራዊ ማድረጓን ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ የኢትዮጵያ የባቡርና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ሪፎርም በማገዝ ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ የባቡር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የነዳጅ ፍጆታን መቀነስና የተሳለጠ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉን ከዓለም የንግድ መስመሮች ጋር በማስተሳሰር የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ባለሀብቶችን በማነቃቃት ሀገራዊ ጥቅል ኢኮኖሚውን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸው፣ ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን በፍጥነት እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚመጥን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሪፎርም መደረጉን ጠቅሰው፣ ለሪፎርሙ ውጤታማነት በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።