የኢሬቻ በዓል በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም 23/2017(ኢዜአ)፦የኢሬቻ በዓል በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳውድ ሙሜ ገለጹ፡፡
ኢሬቻ ከገዳ ስርዓቶች መካከል አንዱ ሲሆን "ኢሬቻ ቱሉ" እና "ኢሬቻ መልካ" በሚል በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል፡፡
"ኢሬቻ ቱሉ" የበጋው ወራት አልቆ በልግ ሲገባ የሚከበር ሲሆን መጪውን ክረምት የዝናብና የአዝመራ አድርግልን በማለት ለፈጣሪ ተማጽኖ የሚቀርብበት ነው፡፡
ሌላኛው "ኢሬቻ መልካ" በአዲስ አበባ "ሆራ ፊንፊኔ" በቢሾፍቱ ደግሞ "ሆራ አርሰዲ" ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ ፈጣሪ ላደረገው መልካም ነገር ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች በሚከበረው በዓል የኦሮሞ ህዝብ ባህል እና ታሪክ በስፋት ይንጸባረቅበታል፡፡
አባገዳዎች፣ ሀደስንቄዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች በባህል አልባሳቶቻቸው እና ጌጣጌጦቻቸው አምረው እና ደምቀው ይታዩበታል።
ይህንን ክብረ በዓል ለመታደም ከአራቱም የኢትዮጵያ አቅጣጫዎች እና ከተለያዩ ክፍላተ-አለማት በርካታ ቁጥር ያላቸው ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኢሬቻ ከምስጋናና ከባህላዊ ክዋኔዎቹ ባሻገር ምን አይነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አለው ሲል የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳውድ ሙሜ ጠይቋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ዳውድ ሙሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢሬቻ የእርቅ፣ የይቅርታ፤ የህብረት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት እና የሰላም መገለጫ ነው::
ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች የበዓሉ አከባበር ደብዝዞ የቆየ እንደነበር አስታውሰው፤ ከለውጡ ወዲህ ግን በአዲስ መልክ በድምቀት መከበር መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በየአመቱ በዚህ በዓል ላይ ለመካፈል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ እና የውጪ አገር ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ለመታደም ወደ አዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ የሚመጡ ወገኖች የኢትዮጵያን አየር መንገድን እንደሚጠቀሙ ጠቅሰዋል፡፡
በቆይታቸውም ሆቴሎችን ጨምሮ ከታናናሽ እስከ ታላላቅ የቢዝነስ ተቋማትን አገልግሎቶች እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከውጪ የሚገቡ የበዓሉ ታዳሚዎች ደግሞ ዶላር ይዘው ስለሚገቡ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውንም እንዲሁ፡፡
በጥቅሉ ኢሬቻ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡
የኢሬቻ በዓልን አሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ ለማክበር በተለይ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የቱሪዝም ፍሰቱን በመጨመርና የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም በዓሉ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለባህላችን ህዳሴ" በሚል መሪ ሀሳብ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡