ዓለምን ከረሃብ ነጻ የማድረግ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በኢትዮጵያ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለምን ከረሃብ ነጻ የማድረግ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በኢትዮጵያ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):- ዓለምን ከረሃብ ነጻ የማድረግ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ከጥቅምት 26 እስከ 28 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) አስታወቀ።
ኮንፍረሱን ያዘጋጁት ዩኒዶ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ በመተባበር ነው።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ለኮንፍረንሱ የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ኮንፍረንስ ዓለምን ከረሃብ ነጻ በማድረግ ጥረት የተገኙ ውጤቶች፣ያገጠሙ ፈተናዎች እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ኢዜአ ከዩኒዶ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተለይም ከእ.አ.አ 2015 አንስቶ ተግባራዊ እየሆነ ባለው የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ግብ (2) እ.አ.አ በ2030 “ዓለምን ምንም ረሃብ የሌለባት” የማድረግ እቅድ አፈጻጸም እንደሚገመገም ተገልጿል።
ከዘላቂ ልማት 17 ግቦች አንዱ የሆነው “ዜሮ ረሃብ” ከዓለም ላይ ረሃብን በማስወገድ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማሻሻል እና ዘላቂ ግብርናን የማጠናከር ትልም ያለው ነው።
በኮንፍረሱ ላይ የቴክኒክ ውይይቶች እና የኢንቨስትመንት ፎረሞችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ተመላክቷል።
ከሁነቶቹ አንዱ የሆነው የከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ፎረም “ዜሮ ረሃብን” ማሳካትን የተመለከተ የጋራ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣ ይጠበቃል።
በኮንፍረንሱ ላይ የአገራት መሪዎች፣የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ንግግር እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
በኮንፍረንሱ ላይ የአገራት መሪዎች፣ሚኒስትሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት፣የግሉ ዘርፍ፣ የፋይናንስ ተቋማትና ምሁራንን ጨምሮ ከ1500 በላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።
የዓለም አቀፍ ኮንፍረንሱ አዘጋጆች መካከል የኢትዮጵያ መንግስት አንዱ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን ሙሐመድ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ተወካዮች ጋር የኮንፍረንሱን ዝግጅት እና የጋራ ስራዎችን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።