ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ወልቂጤ ከተማን በፎርፌ አሸንፎ የነበረ ቢሆንም ወልቂጤ ከሊጉ መሰረዙን ተከትሎ የፎርፌ ውጤቱ መሰረዙ ይታወቃል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ንግድ ባንክ በመጀመሪያ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ጋር በነበረው የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል።

ቡድኑ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታል።

በበረከት ደሙ የሚሰለጥነው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ክለቡ በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል።

የፕሪሚየር ሊጉ የሶስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሲዳማ ቡና መካከል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አጋጥሞታል።

በሁለቱ ጨዋታዎች አንድ ግብ ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።

በዘላለም ሽፈራው የሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና በበኩሉ በሊጉ ባከናወናቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።

ክለቡ በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ሃዋሳ ከተማን እንዲሁም መቻል ወላይታ ድቻን በተመሳሳይ 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም