ብርሸለቆ ከሀገር ዘቦች ማዕከልነት ባሻገር

በምዕራብ ጎጃም ዞን የብር ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ ገባውን በተራራማ ገመገሞች የተከበበ ሸለቋማ ስፍራ ነው ብር ሸለቆ።

በትርፍ አምራችነታቸው የሚታወቁትን የጃቢጠህናን እና የቡሬ የቆላ ዳሞት ወረዳዎችን የሚያካልለው ብር ሸለቆ፤ በ1978 ዓ.ም ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል መቋቋሙ ለአካባቢው ልማት እንቅስቃሴ መዳበር የራሱን አወንታዊ ሚና ተጫወቷል።

ቀኑን ሙሉ ቢዞሩት የሚዘልቁት የማይመስለው የብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ከ32 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚሸፍኑ የማዕከሉ ወታደራዊ መኮንኖች ይናገራሉ።

ማሰልጠኛ ማዕከሉ ባለፉት አስርት ዓመታት አገልግሎቱ ከ40 ዙር በላይ ሰልጣኞችን በማስመረቅ በየዘመኑ ለሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ዘብ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ወጥተውበታል፣ ዛሬም እልፍ ወታደሮችን እያፈራ ነው።

የብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የሚገኝበት ስነ ምህዳር ለምርት የተመቸና መልከ ብዙ ዕድሎች ያሉት ቢሆንም እስካሁን ይህን ዕድል ሳይጠቀም ቆይቷል።

አሁን ግን እንደ ሀገር የተያያዘውን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ አጀንዳ በመከተል በ2016 ዓ.ም የመኸር ወቅት በጥምር ግብርና ልማት ተሰማርቷል።

በማዕከሉ የጥምር ግብርና ልማት ኃላፊ ሻለቃ ሀብቱ ገብረሥላሴ እንደሚሉት በዚህ የምርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ሰብሎች 21 ሄክታር መሬት አልምቷል።

ከነዚህ መካከል 19 ሄክታሩ ቦቆሎ ሲሆን ቀሪው የሽንኩርት፣ የበርበሬ እና ሌሎች ሰብሎች መሆናቸው ተናግረዋል።

ማዕከሉ እንደ ተቋምና እንደ ሀገር የተያዘውን በምግብ ራስን የመቻል ጥረት በመከተል ወደ ስራ መግባቱን ገልፀዋል።

በዚህም ከሰብል ልማት ባሻገር በወተት ላም፣ በዶሮ፣ በበግና ፍየል እርባታ ሰፋፊ ስራዎችን ጀምሯል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም