በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው - ብሔራዊ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅሞ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው - ብሔራዊ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):- በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ብሔራዊ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ በሊባኖስ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።
የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ባለው ዝግጅት
ላይ የመከረ ሲሆን በቤይሩት የሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እያካሄደ ያለውን የዜጎች ምዝገባ ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሟል።
ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤቱ እያደረገ ያለውን ምዝገባ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሰፊ ርብርብ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኮሚቴው በሊባኖስ ወቅታዊ ሁኔታ ደኀንነታቸው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የተገኙ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው ብለዋል።
ይህን የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ በተሻለ ፍጥነት መከወን እንዲቻል ተጨማሪ የሰው ኃይል ወደ ቤይሩት እንደሚላክም ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤቱ ባዘጋጀው አድራሻ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምዝገባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በቀጣይም መንግሥት ለዜጎች በሚደረገው ክትትል እና ድጋፍ ዙሪያ በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አደረጃጀቶች በኩል መረጃ እንደሚያደርስ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።