የፓን አፍሪካ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፍረንስ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የፓን አፍሪካ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፍረንስ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):- ሶስተኛው የፓን አፍሪካ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፍረንስ መስከረም 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢኒስቲትዩቱ ያዘጋጀው ኮንፍረንስ “ለአፍሪካ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ተጨማሪ አቅም መፍጠር” በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ኮንፍረንሱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ትብብር፣ ኢኖቬሽንና የእውቀት ሽግግር ማጎልበት አላማ ማድረጉን የኢኒስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በኮንፍረንሱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምሁራን በአፍሪካ በዘርፉ ያሉ ጠቀሜታዎች፣ ፈተናዎች እና ቀጣይ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱ ሳይንሳዊ ጽሁፎችን እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል።
በጥናታዊ ጽሁፎቹ ቴክኖሎጂው በጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ፋይናንስ፣ ዲጂታል አገልግሎቶች እና በተለያዩ መስኮች ያለውን ጠቀሜታ እንደሚዳሰስ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔዎች መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተካሄዱት ሁለት ኮንፍረንሶች የተገኙ ተሞክሮዎችን እንደሚገመገሙም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላትን ተሞክሮዎች በፎረሙ ላይ እንደምታቀርብም እንዲሁ።
በኮንፍረንሱ ላይ የአገር ውስጥ እንዲሁም አህጉር አቀፍ ዓለም አቀፍ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማት፣ተመራማሪዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች እና ተማሪዎች እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ቴክኖሎጂው በአገሪቷ እንዲታወቅ፣ ግንዛቤ እንዲኖር እንዲሁም ዳታን መሰረት ያደረጉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎች ለኢትዮጵያ ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻል እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ ተጠቃሚነትን የማሳደግ እና ለጀማሪ አልሚዎች ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ስራዎች በማከናወን የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን በመግለጽ።
ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂዎችን ለስማርት ሲቲ ፕሮጀክት፣ አገርኛ ቋንቋዎችን የማሽን ቋንቋ ለማድረግ፣ ለስማርት ፍርድ ቤቶች፣ ግብርና፣ ጤና፣ ፋይናንስ፣ ወንጀልን መከላከልና በተለያዩ መስኮች ጥቅም ላይ እያወለች መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ በዘርፉ ኢትዮጵያን ይበልጥ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በትኩረት እንደሚከናወን አክለዋል።