የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል - አቶ አህመድ ሺዴ - ኢዜአ አማርኛ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል - አቶ አህመድ ሺዴ
አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ሁለት ወራት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ገለጹ።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው እለት ተገምግሟል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ያለፉት ሁለት ወራት አፈጻጸም በዝርዝር መገምገሙን በተለየም ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዚህም ማሻሻያው ኢኮኖሚው በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ከማድረጉም ባሻገር በዜጎች ላይ የሚፈጠርን ማህበራዊ ጫና በቀነስ አግባብ መተግበሩን ነው ያነሱት፡፡
በቅርቡም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን በማሻሻያው አፈጻጸም ላይ ግምገማ በማካሄድ በተሳካ መልኩ እየተተገበረ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋነኛ ትኩረት የመንግስትን ገቢ ማሻሻል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።
በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ ገቢ መገኘቱን ነው ያብራሩት፡፡
በቀጣይም የመንግስት ገቢን የማሳደጉ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አቅጣጫ መቀመጡን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የገቢ ማሻሻያውን በሚመለከትም ከግብር ከፋዮች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት አስቀድሞ የዝግጅት ስራ በማከናወን ወደ ትግበራ መግባቱንም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ከመስከረም ጀምሮ የሚተገበር የደሞዝ ጭማሪ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
መንግስት ዘይት በድጎማ እንዲገባ ማድረጉንና የማዳበሪያ ድጎማውም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
በከተማና ገጠር ለሚተገበር የማህበራዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብርም መንግስት 60 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት በመያዝ ተጨማሪ ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው የእዳ ሽግሽግ ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ንግድ ባንክ ለተለያዩ የልማት ድርጅቶች አብድሮት የቆየውና ያልተከፈለን እዳ ለማሸጋሸግና ለካፒታል እድገት ጭማሪ በገንዘብ ሚኒስትር በኩል እስከ ዘጠኝ መቶ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቦንድ ለንግድ ባንክ ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡
በትሬዥሪ ቢል አመካኝነትም ለረዥም ጊዜ ያልተከፈሉ ብድሮች ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ እንዲቀየሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ሀገር የብድር ሽግሽግን በሚመለከትም በቡድን 20 የተቋቋመው የአበዳሪ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የብድር ማሸጋሸግ ዋስትና መስጠቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ የውጭ እዳ ትፎይታ እንደምታገኝ ጠቁመዋል፡፡
ከልማት አጋሮች ጋር የሚደረገው ውይይትም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡