ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በመደረጉ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመትም ኢትዮጵያ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ልታስመዘግብ የምትችልበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የ8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አስምዝግቧል ብለዋል።

በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ምእራፍ አንድ ለግብርና እና አምራች ኢንዳስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ለጥቅል ሀገራዊ ዕድገቱ እምርታዊ ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል።

በዚህም ዋና ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚባሉት ግብርና 6 ነጥብ 9 በመቶ፣ ኢንዳስትሪ 9 ነጥብ 2 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፍ 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ገልጸተዋል።

በተመዘገበው ዕድገት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማነቆ የነበረው የሲሚንቶ ችግር መፍትሔ በማግኘቱ የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በመደረጉ በ2017 ዓ.ም ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ ይችላል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው በገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር የተሻለ ፍሰት እንዲፈጠር በማድረግ ወጪ ንግድ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በምንዛሬ ተመን ጅምር ውጤት ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ የላቀ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።

የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ተዋናዮችን ተወዳዳሪነት በማሳደግ የአልሚ ባለሃብቶችን ተጠቃሚነት ለማሳለጥም እንዲሁ።

የግብርና እና የኢንዳስትሪ የገበያ አቅርቦት ፍላጎቶችን በመሙላት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የራሱ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻው የዜጎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን መደጎም የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም