ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ራሄል ጌታቸው ጋር ተፈራርመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ አየር መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በርካታ ተጓዦችን በማመላለስ እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፉን በመደገፍ ከፍተኛ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የሚያልፉ ተጓዦች ለቱሪስቶች የሚቀርቡ ቁሶችን ገዝተው እንደሚሄዱና ይህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ ድርጅቱ የሽያጭ አገልግሎት የሚሰጥበትን የገበያ ማዕከል መሰረተ ልማት በመገንባት ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ የአገር ውስጥ ምርትን በማስተዋወቅ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ስራ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ራሄል ጌታቸው በበኩላቸው ድርጅቱ ላለፉት 60 አመታት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ የመጀመሪያ የሆነና ከቀረጥ ነጻ የመገበያያ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ግንባታው ከአየር መንገዱ ካርጎ አጠገብ በሚገኝ 14 ሺህ 539 ካሬ መሬት ላይ የሚያርፍና በ 4 ነጥብ 3 ቢልየን ብር የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገሪቱ ቱሪዝም እንዲያድግ ሲሰራ መቆየቱን እና አሁንም እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአየር ትራንስፖርት እና ቱሪዝም በጥብቅ የተሳሰሩ በመሆናቸው ስምምነቱ የቱሪዝም ዘርፉን በጋራ ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማቱ የስራ ኃላፊዎች ለስምምነቱ ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም