የኢሬቻ በዓል የመደጋገፍ፣የአንድነት፣የፍቅር፣የእርቅና ሰላም ማሳያ በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ማስቀጠል ይገባል-አባገዳዎች

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦የኢሬቻ በዓል የመደጋገፍ የአንድነት፣የፍቅር፣የእርቅና ሰላም ማሳያ በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ አባገዳዎች ተናገሩ።

የኢሬቻ በዓል መስከረም 25 በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በቀጣዩ ቀን በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል።

የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል የሀገራዊ አንድነት፣ የእርቅና የአብሮነት ማሳያ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኃብት በመሆኑ በየዓመቱ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረም ይገኛል።

የሀገር ኃብት የሆነው ኢሬቻ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን፤ አንዱ የተራራ ኢሬቻ (ኢሬቻ ቱሉ) የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት የሚከናወን ይሆናል።

ሁለተኛው ደግሞ የመልካ (የውኃ ዳር) ኢሬቻ በመስከረም ወር አጋማሽ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይከበራል።

የበዓሉን አከባበር በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው አባገዳ ተክሉ ጉደታ፤ የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነትና የይቅርታ እሴትን የሰነቀ ታላቅ በዓል መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ይህንን ትልቅ የሀገር እሴትና ኃብት ጠብቆ በማስቀጠል ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

 

አባገዳ ጫሎ ዋጆ በበኩላቸው፤የኢሬቻ በዓል ሲከበር አብሮነትን፣ ሰላምንና ሀገራዊ አንድነትን መሠረት ባደረገ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል።


 

አባገዳ ደሳለኝ ፈይሳ በበኩላቸው፤ታላቁን የኢሬቻ በዓል ስናከብር ሰላምን በማስቀደም አንድነትን፣ አብሮነትንና መደጋገፍን በማሳየት መሆን አለበት ብለዋል።

የኢሬቻ በዓል አንዱ የገዳ ሥርዓት መገለጫ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳደስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም