ቀጥታ፡

በደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው የተጠናከረ ዝናብ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው የተጠናከረ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት በቀጣዮቹ ቀናት የሚጠበቁ የአየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎችን በተመለከተ ለኢዜአ የፅሁፍ ማብራሪያ ልኳል።

በዚህም መሰረት በቀጣዮቹ አስር ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት እድገታቸውን ላልጨረሱና ለቋሚ ተክሎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ አስታውቋል።

ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት ደቡባዊው የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮችም ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጠቀሜታ አለው ተብሏል።

በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለው ዝናብ ቀጣይነት እንደሚኖረው በኢንስቲትዩቱ ትንበያ ተመላክቷል።

በደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተጠናከረ ሁኔታ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው እንደሚሆንም አስታውቋል።

የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ጎልቶ እየታየ በመሆኑ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ በሀገሪቱ የሰሜን አጋማሽ ክፍሎች እንደሚጨምርም ይጠበቃል።

የምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቷ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ተመላክቷል።

በአብዛኛው ባሮ አኮቦ የታችኛውና የመካከለኛው አባይ፣ ኦሞ ጊቤ፤ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ እስከ ከፍተኛ የሚደርስ የእርጥበት መጠን የሚኖር ይሆናል።

በዚህም የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውኃ ሀብትን ከማጎልበት አንጻር የጎላ ጠቀሜታ የሚኖረው ሲሆን የመስኖም ሆነ የሀይል ማመንጫ ግድቦችን የውኃ መጠን ከፍ እንደሚያደርግ ተገምቷል።

የታችኛውና የመካከለኛው ዋቤ ሸበሌ እና የገናሌ ዳዋ በአንጻሩ መጠነኛ የሆነ የእርጥበት መጠን እንደሚያገኙም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም