የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለማግኘትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለማግኘትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):-የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም መረጃዎችን በተደራጀ መልኩ ለማግኘትና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ማህበራት ገለጹ፡፡
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንቱ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም በዓድዋ ሙዚየም ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ከቱሪዝም ባሻገር ለግብርናና ለኮንስትራክሽን ዘርፎች መነቃቃት የሚያግዝ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቱሪዝምና ስታቲስቲክስ ክፍል፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የስታቲስቲክስ ማዕቀፍ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበራት እንዳሉት፤ ሂደቱ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት ነው፡፡
አካውንቱ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ተገንዝቦ ለመተንተን እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻ እና ስልታዊ የእቅድ ዝግጅትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኝ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ኤንዲ አሰፋ እንዳሉት፤ሳተላይት አካውንቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የመረጃ አያያዝ ክፍተት ለመሙላት እድል የሚፈጥር ነው ፡፡
በተለይም የቱሪስቶችን ፍላጎት በመለየት ቀድሞ ለመዘጋጀት፤ያልተሟሉ መሰረተ ልማቶችንም ወይንም የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን ቀድሞ ለመስራት የሚያግዝ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አሸናፊ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደገለጹት ፤ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መሆን ቱሪስቶች በቀላሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና የሆቴል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ፣የተቋማትንና የአገልግሎት ሰጪዎችን የተቀናጀ አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ የራሱ የሆነ አወንታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡